ቀጥታ፡

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሪፖርቱ እውነትን በማውጣት አዲስ አቋም ያሳየበት መሆኑን ምሁራን ገለጹ

ባህር ዳር (ኢዜአ) የካቲት 12/2014--አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው ሪፖርት በይዘት፣ በጥልቀትና በቦታ ሽፋን የተሟላ ባይሆንም በቆቦና ጭና አካባቢዎች በአሸባሪው ህወሓት የተፈጸሙ ወንጀሎችን ይፋ ማድረጉ እውነታውን ለዓለም ማህበረሰብ በማሳወቅ አዲስ አቋም ያሳየበት ነው ሲሉ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።

ረዳት ፕሮፌሰር ምስጋናው ጋሻው በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር ሲሆኑ፤አሸባሪው ህወሓት በንጹህን ዜጎች ላይ የፈጸመውን ግፍ ለማወቅ ዩኒቨርሲቲው ባካሄደው ጥናት ከተሳተፉት ምሁራን አንዱ ናቸው።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል  በቆቦና ጭና አካባቢዎች በአሸባሪው ህወሓት የተፈጸሙ ወንጀሎችን ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ሪፖርት ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር ምስጋናው ጋሻው እንዳሉት፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አሸባሪውን ህወሓት ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል እውነታውን የዳሰሰ ሪፖርት ማውጣቱ የሚበረታታ ነው።

ቀደም ሲል የኢትዮጵያን መንግሥት የሚቃረን ሪፖርት ያወጣ እንደነበር አስታውሰው፣"በቃለ መጠይቅ፣ በሳተ ላይት ምልከታና ሌሎች ዘዴዎችን ተጠቅሞ ሰሞኑን ያወጣው ሪፖርት ተቀባይነት አለው" ብለዋል።

ረዳት ፕሮፌሰሩ እንዳሉት ሪፖርቱ በቆቦ እና ጭና አካባቢዎች አሸባሪው ህወሓት ባልታጠቁ ንጹሀን ዜጎች ላይ የፈጸመውን የጅምላ ግድያ፣ የአስገድዶ መድፈርና ፆታዊ ጥቃት እንዲሁም በንብረት ላይ ያደረሰውን ውድመት ለዓለም ህዝብ ያጋለጠ ነው።

"ምንም እንኳ ሪፖርቱ በይዘት፣ በጥልቀትና በቦታ ሽፋን የተሟላ ነው ባይባልም ተቋሙ ከዚህ በፊት ሲያወጣቸው ከነበሩት ጋር ሲነጻጸር አዲስ አቋም እየያዘ መምጣቱን ያሳያል" ብለዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር ምስጋናው እንዳሉት አሸባሪ ቡድኑ በማይካድራ፣ ጋሊኮማ፣ አጋምሳ፣ ጋሸና፣ መርሳ፣ አንጾኪያና ሌሎች የሰሜን ሸዋ፣ ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ኦሮሚያ ልዩ ዞንና ሰሜን ጎንደር አካባቢዎች ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በንጹሀን ላይ የጅምላ ጭፍጨፋና ሌሎች ወንጀሎችን ፈጽሟል።

ሪፖርቱ በቆቦ እና ጭና አካባቢዎች በአሸባሪው ህወሓት የተፈጸመውን ግፍ ይዞ መውጣቱ አሸባሪውን ቡድን በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በጦር ወንጀል ለመጠየቅ የሚያስችል ነው።

ይሁንና የአሸባሪ ቡድኑ ዓላማ ንጹሀንን ከመግደልና ሃብት ከመዝረፍ ባለፈ መውሰድ ያልቻለውን ንብረት በሙሉ አውድሞ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ማድረስ ስለሆነ ይህም በሪፖርቱ በስፋት መዳሰስ እንደነበረበት ምሁሩ ተናግረዋል።

ሌላው የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ደሳለኝ ጥጋቡ በበኩላቸው እንዳሉት፣ አምነስቲ በደረሰበት ልክ እንጂ በአሸባሪው ከደረሰው ጉዳት አንጻር በሪፖርቱ የተገለጸው በቂ ነው ተብሎ አይወሰድም።

"ይሁን እንጂ እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አይነት ያሉ ተቋማት እንደ አሁኑ ሚዛናዊና ሳይንሳዊ የሆነ ጥናት አካሂደው ሲያቀርቡ ሪፖርቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያስገኛል" ብለዋል።

በሀገራችን እንደዚህ አይነት አሰቃቂና አሳፋሪ ድርጊት ለወደፊት እንዳይከሰት ትምህርት የሚወሰድበት በመሆኑ ከሌሎች ጥናቶች ጋር በማዳመር ሰንዶ ለታሪክ ለማስቀመጥ እንደሚያግዝም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅና ግንዛቤ እንዲያዝ በማድረግ የሽብር ቡድኑን ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚያስችልም ረዳት ፕሮፌሰር ደሳለኝ አመልክተዋል።

እንደ ምሁሩ ገለጻ በቀጣይም መንግሥት እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያሉ ድርጅቶች ጉዳት በተፈጸመባቸው አካባቢዎች ገብተው በማጥናት እውነታውን ለዓለም ህዝብ እንዲያሳዩ ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሳምንቱ መጀመሪያ ባወጣው ሪፖርት የአሸባሪው ህወሓት አባላት በአማራ ክልል ከተሞች የሚገኙ በርካታ ንጹሀን ሰዎችን ሆነ ብለው መግደላቸውን፣ ሴቶችና ታዳጊዎችን አስገድደው በቡድን መድፈራቸውን እንዲሁም የግልና የህዝብ ንብረት ማውደማቸውን መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡

የሽብር ቡድኑ ወሯቸው በነበሩ የክልሉ አካባቢዎች ዓለም አቀፍ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት ሕጎችን አለማክበሩንም በሪፖርቱ አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም