የዘንድሮው የአድዋ ድል በዓል "አድዋ ለኢትዮጵያውያን ኅብረት የአፍሪካ የነፃነት ጮራ’’ በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል

638

የካቲት 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአድዋ ድል በዓል "አድዋ ለኢትዮጵያውያን ኅብረት የአፍሪካ የነፃነት ጮራ’’ በሚል መሪ ኃሳብ በተለያዩ መርኃ ግብሮች እንደሚከበር የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።

ዘንድሮ ለ126ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአድዋ ድል በዓል አከባበር በሚመለከት የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ መግለጫ ሰጥተዋል።

"የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፤ የመላ አፍሪካዊያን ነው" ያሉት ሚኒስትሩ ዘንድሮ" አድዋ ለኢትዮጵያውያን ኅብረት የአፍሪካ የነፃነት ጮራ’’ በሚል መሪ ኃሳብ እናከብረዋለን ብለዋል።

በአድዋ ጦርነት ወራሪው የጣሊያን ጦር ሽንፈትን ተከናንቦ የተመለሰበት መሆኑን አውስተው፤ ድሉ የመላ ጥቁር ህዝቦች የአሸናፊነት ተምሳሌት ነው ብለዋል።

በመሆኑም የዘንድሮው የአደዋ ድል በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

እለቱን በፓናል ውይይቶች፣ አውደ ርዕይ በማዘጋጀት፣ ኪነ-ጥበባዊ ዝግጅቶችና ሲምፖዚየም ጭምር በማካሄድ ይከናወናል ብለዋል ሚኒስትሩ።

በዓሉ ከየካቲት 15 እስከ 23 ቀን 2014 ዓ.ም በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ሚሲዮኖች ጭምር እንደሚከበር ጠቁመዋል።  

የአድዋ ድል በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር ቀኝ ገዢዎች በጥቁር ሕዝብ ተሸንፈው ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካ የነፃነት አዲስ ምዕራፍ የከፈቱበት ታሪካዊ በዓል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም