ፌዴሬሽኑ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች የ150 ሚሊዮን ብር የአይነት ድጋፍ አሰባሰበ

76

የካቲት 12/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን በአማራና አፋር ክልሎች በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች  ድጋፍ የሚውል የ150 ሚሊዮን ብር የአይነት ድጋፍ ማሰባሰቡን ገለጸ።

በቀጣይም እነዚህን ቁሳቁሶች ለተጎጂዎቹ የማድረስ ሥራ እንደሚሰራ ተገልጿል።


የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን በአማራና አፋር ክልሎች በጦርነቱ ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም ከህዳር 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ወራት የሚቆይ አገራዊ ንቅናቄ መጀመሩ ይታወሳል።

በተካሄደው ንቅናቄ  ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ  የአይነት ድጋፍ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መሰብሰብ መቻሉን የፌዴሬሽኑ ዋና ጸኃፊ ኤርሚያስ ማቴዎስ ገልጸዋል።

በቀጣይም እነዚህን ቁሳቁሶች ለተጎጂዎቹ የማድረስ ሥራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በንቅናቄው በሁሉም ክልሎች የሚገኙ ከ10 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች መሳተፋቸውን ነው የገለጹት።

ከመልሶ ማቋቋም በተጨማሪ በአጎራባች ክልልች መካከል ያሉ ግጭቶችን በቋሚነት ለመፍታት የወጣቱ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ወጣቱ ተደራጅቶ አካባቢውን መጠበቅ በመቻሉ ኅብረተሰቡ የደህንነት ስሜት እንዲሰማው በማድረግ ለአገሩ ዘብ መሆኑን አስመስክሯል ብለዋል።

ወጣቱ በሁሉም ክልሎች ባደረገው ምክክር ሰላምን በማስጠበቅ ረገድ ሰፊ ሥራ መሰራቱንም ተናግረዋል።

የፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙረዲን ናስር በበኩላቸው፤ ወጣቶች የገንዘብ ድጋፍ ከማድረጋቸው በተጨማሪ ግንባር ድረስ የዘመቱ ወጣቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን ወጣቶቹ የዘማች ቤተሰቦችን አዝመራ ከመሰብሰብ ጀምሮ ሌሎች በርካታ አስተዋጾዎችን  ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት።

ፌደሬሽኑ ወጣቶቹ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው በመቀጠል የድርሻቸውን ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም