ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በቲካድ ስብሰባ ላይ እንድትሳተፍ ተጋበዘች

አዲስ አበባ ነሃሴ 26/2010 የጃፓን መንግስት በመጪው ጥቅምት በጃፓን በሚካሄደው የቶክዮ-አፍሪካ ልማት ፈንድ ዓለምዓቀፍ የሚኒስትሮች ስብሰባ (ቲካድ) ላይ ኢትዮጵያ እንድትሳተፍ ጥሪ አቀረበ። የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ አማካሪ ኬንታሮ ሶኑራ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ጋር በተገናኙበት ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በስብሰባው ላይ እንዲሳተፉ ከአገራቸው አቻ የመንግስት ኃላፊ የተላከውን የግብዣ መልዕክት አቅርበዋል። በመሪዎች ደረጃም የዛሬ ዓመት ገደማ በሚካሄደው ተመሳሳይ ስብሰባ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራ የኢትዮጵያ ልዑክ እንዲገኝም ከወዲሁ ከአገራቸው የበላይ አመራር የተላከውን የግብዣ መልዕክት አስተላልፈዋል። ኢትዮጵያና ጃፓን በመሰረተ-ልማት ግንባታና በካይዘን ስራ አመራርና አቅም ግንባታ ውጤታማ ትብብሮች አድርገዋል። ከሁለትዮሽ ትብብር በተጨማሪ በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና በቶኪዮ-አፍሪካ ልማት ፈንድ /ቲካድ/ ማዕቀፍ ስር ይተባበራሉ። የጃፓን ባለሃብቶች የራሳቸውን የኢንዱስትሪ ዞን በኢትዮጵያ እንዲከፍቱ ማድረግን ጨምሮ የሁለቱን አገራት የኢኮኖሚ ትብብር ለማፋጠን የሚያስችል የጋራ ስምምነት ለመፈራረም ድርድሮች ተጀምረዋል። የአሁኑ የጃፓን ልዑክ ጉብኝት ዓላማም ስምምነቱን በአጭር ጊዜ መፈራረም በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። ከዚህ ጎን ለጎን በጉዳዩ ላይ አዲስ አበባ ከሚገኙት የጃፓን ኤምባሲ፣ የጃፓን የውጭ ንግድ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት (ጄትሮ) እና ከጃፓን የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ጋር በቅርበት እየተሰራ ይገኛል። ኢትዮጵያና ጃፓን ከ85 ዓመታት በላይ የዘለቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን ከ240 በላይ ጃፓናዊያን በኢትዮጵያ የተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም