በኢትዮጵያ የመንግስት ሠራተኞች የሃብት ምዝገባ በኢንተርኔት መከናወን ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የመንግስት ሠራተኞች የሃብት ምዝገባ በኢንተርኔት መከናወን ጀመረ
የካቲት 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የመንግስት ሠራተኞች የሃብት ምዝገባ በበይነ-መረብ /ኢንተርኔት/ መከናወን ጀመረ።
የፌዴራል ስነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የመንግስት ሠራተኞችን የሃብት ምዝገባ በበይነ-መረብ (ኢንተርኔት) ማከናወን ጀምሯል።
ኮሚሽኑ በቴክኖሎጂ የታገዘ የቀጥታ የሀብት ምዝገባ ዝርጋታ አጠናቆ የመጀመሪያውን የሀብት ምዝገባ በተቋሙ አመራሮች እና ሠራተኞች ላይ በዛሬው እለት አስጀምሯል፡፡
ከዚህ በፊት ይከናወንበት ከነበረው የማንዋል አሰራር በመውጣት ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል አሰራር መግባቱንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በኮሚሽኑ የሃብት ማሳወቂያ እና ምዝገባ ዳይሬክተር መስፍን በላይነህ እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ አዲስ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ምዝገባውን በኦንላይን እና በኦፍላይን ማካሄድ እንደሚቻልም ገልጸዋል።
ሃብት አስመዝጋቢዎች ባሉበት ቦታ ሆነው በኤሌክትሮኒክስ አማራጭ በመጠቀም መመዝገብ እንዲችሉ ታሳቢ ተደርጎ የተጀመረ አሰራር መሆኑንም አስረድተዋል።
በበይነ-መረብ (ኢንተርኔት) የሚከናወነው ምዝገባ ሥራውን ከሲስተም ጋር በማያያዝ ከዚህ በፊት የነበረውን የማንዋል አሰራርና የመረጃ አያያዝ ጥራት ችግር ለማስወገድ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተጠቁሟል።
የሃብት ማሳወቅ እና ምዝገባ ሥርዓቱን የፌዴራልና የክልል መንግስታት በተዘረጋው ዲጂታል አሰራር መጠቀም እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡
በመሆኑም ሁሉም የመንግስት ተቋማትና የመንግስት የልማት ድርጅቶች በቀጣዮቹ ሦስት ወራት ውስጥ ከየካቲት 21 እስከ ሚያዝያ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ምዝገባቸውን ማጠናቀቅ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።