ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ ሁሉም ቤተ እምነቶች ለተከታዮቻቸው የሰላምን አስፈላጊነት ማስተማር ቀዳሚ ተግባራቸው ሊያደርጉ ይገባል

በኢትዮጵያ የሚገኙ ሁሉም ቤተ እምነቶች ለተከታዮቻቸው የሰላምን አስፈላጊነት ማስተማር ቀዳሚ ተግባራቸው ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የሃይማኖት አባቶች እንደገለጹት በኢትዮጵያ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሃይማኖትና ብሔር መልክ ያላቸው ግጭቶች በስፋት እየተስተዋሉ መጥተዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶች እየተባባሱ ለበርካታ ሰዎች ሞትና ጉዳት እንዲሁም የንብረት ውድመት ምክንያት መሆናቸውን አስታውሰው ድርጊቱ በየትኛውም ሃይማኖት የሚወገዝና ፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስረድተዋል።

እንዲህ አይነት ድርጊቶች የሚፈፀሙት በምእነትና ማንነት ሰበብ የጥፋት ዓላማ በያዙ ግለሰቦች በመሆኑ የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ ሊቀበለው አይችልም ነው ያሉት አባቶቹ።

በመሆኑም በኢትዮጵያ የሚገኙ ሁሉም ቤተ እምነቶች ለተከታቶቻቸው የሰላምን አስፈላጊነት ማስተማር ቀዳሚ ተግባራቸው ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባት መላዕከ ጸሃይ አባ ወልደብርሃን ገብረ መድህን፤ የሃይማኖት መሪዎች ለሚከተላቸው ህዝብ ምን ጊዜም ሰላምን ማስተማር ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

በአንድ አገር ውስጥ ሰላም ከሌለ ሁሉም ነገር የሚበላሽ በመሆኑ ሰላም የምንም ነገር መሰረት መሆኑን ሁላችንም በጥሞና ልንረዳው ይገባል ነው ያሉት።

"ወንጌል ማለት ሰላም ማለት በመሆኑ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስለ ሰላም ማስተማርና በቂ ግንዛቤ መፍጠር የእኛ የእምነት አባቶች የእለት ተዕለት ስራችን መሆን አለበት" ብለዋል፡፡

በሃይማኖት ሽፋን በህዝብ ዘንድ ግጭት ለመፍጠር የሚሰሩ አካላትን ማጋለጥ የሁሉም ሃላፊነት ሆኖ መንግስትም በአጥፊዎች ላይ እርምጃ ሊወስድ ይገባል ነው ያሉት።

በተለይም ወጣቱን ትውልድ በመልካም ስነ ምግባር ከመቅረጽ አኳያ የሃይማኖት አባቶች ትኩረት ሰጥተን ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ያሉት ደግሞ የቃለ-ህይወት ቤተክርስቲያ ቄስ ዶክተር ታረቀኝ ያዕቆብ ናቸው፡፡

ፈጣሪውን የሚፈራ ትውልድ የሰላም ተምሳሌት የመልካምነት መገለጫ ሆኖ የአገርና ህዝብ አለኝታ ስለሚሆን በዚህ ዙሪያ የሃይማኖት አባቶች ሃላፊነታችንን በአግባቡ እንወጣ ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከአዲስ አበባ ነጃሺ መስጂድ ሼህ ሬድዋን ለለምዳ፤ በአገር ሰርቶ ለመኖርና በእምነቱ ጸንቶ በመዝለቅ ፈጣሪውን ለማመስገን እንዲችል የሁሉም ዋስትና ሰላም መሆኑን ይናገራሉ።

በመሆኑም ሁላችንም በሰላም እንድንኖር የኢትዮጵያ ሰላም የህዝቦች አብሮነት ወሳኝ በመሆኑ የእምነት አባቶች አስተምህሮ ትልቅ ዋጋ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም