ድርጅቱ ከ1 ሺህ በላይ ለችግር የተጋለጡ ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ

ሆሳዕና ፤ የካቲት 11/2014(ኢዜአ) ኤስ ኦ ኤስ የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በሆሳዕና ከተማ ከ1 ሺህ በላይ ለችግር የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የ60 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ዛሬ ይፋ አደረገ።

በሥነ-ሥርዓት ላይ  የድርጅቱ የደቡብና ሲዳማ ክልሎች ፕሮግራም አስተባባሪ  አቶ ፀጋዬ ደጀኔ፤ድርጅቱ ከ1996ዓ.ም ጀምሮ ለተለያየ ችግር የተጋለጡ ዜጎችን እየደገፈ ይገኛል ብለዋል ።

ድጋፉ በተለይም ህፃናት፣ወጣቶችንና የአካል ጉዳተኛ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናግረዋል።

ዛሬ ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት በሆሳዕና ከተማ ከ1 ሺህ በላይ የሆኑ ለችግር የተጋለጡ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አስታውቀዋል ።

ህፃናትን በትምህርትና በቁሳቁስ መደገፍ፤ቋሚ የስራ እድል መፍጠር እንዲሁም ጧሪ የሌላቸው አረጋዊያን የሚደረግ እንክብካቤ ፕሮጀክቱ ከሚያተኩርባቸው ተግባራት ውስጥ ይገኙበታል።

በተጨማሪ ሁለት  እድሮችን እንደሚደገፍም ጠቁመዋል።

ለሶስት ዓመታት በስራው ለሚቆየው ፕሮጀክቱ   ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደረግበት መሆኑን ነው ያስታወቁት።

የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብርሃም መጫ በበኩላቸው፤  ለተለያየ ችግር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ ድርጅቱ ላሳየው በጎ ተነሳሽነት ምስጋና አቅርበዋል ።

በቀጣይም ከፍተኛ ችግር ላይ ያሉ ዜጎችን በመለየት ከድጋፍ ባሻገር ቋሚ የስራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ለማስቻል ከድርጅቱ ጋር በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል ።

የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አማካሪ አቶ ገብረየስ ጡሞሮ፤ ፕሮጀክቱ ለተለያየ ችግር የተጋለጡ ዜጎችን በመደገፍ ረገድ ያለውን ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል ።

በተለይም ፕሮጀክቱ የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑና በተለያዩ ምክንያቶች መማር ያልቻሉ ህጻናት የሚደግፍ መሆኑ ልዩ ትርጉም የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ለስራ ስኬታማነት  አስተዳደሩ እንደሚደግፍ አስታወቀዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሀድያና ስልጤ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መላከ ህይወት ቀሲስ ንጉሴ ባወቀ ፤ ድርጅቱ አቅም የሌላቸውን ማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ለማድረግ ያሳየው መነሳሳት የሚደገፍና የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ ምክንይቶች ለችግር  የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች መደገፍና ማብቃት ለመንግስት ወይም ለተወሰነ አካል የሚተው አይደለም ያሉት መላከ ህይወት ቀሲስ ንጉሴ፤ ተጋግዘን ከችግር የመውጣት ባህል መንፈሳዊ እርካታ የሚሰጥ በመሆኑ መጠናከር አለበት ብለዋል።

በመርሐ ግብሩ የሀዲያ ዞንና የሆሳዕና የከተማ አስተዳደር የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፤የሀገር ሽማግሌዎች፤ የኃይማኖት አባቶችና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም