በሀላባ ቁሊቶ በህገ ወጥ መንገድ የተከማቸ ከ6 ሺህ ሊትር በላይ ቤንዚን ተያዘ - ኢዜአ አማርኛ
በሀላባ ቁሊቶ በህገ ወጥ መንገድ የተከማቸ ከ6 ሺህ ሊትር በላይ ቤንዚን ተያዘ
ሆሳዕና የካቲት 11/2014 (ኢዜአ)... በሀላባ ቁሊቶ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ በግለሰብ ቤት የተከማቸ ከ6 ሺህ 500 ሊትር በላይ ቤንዚን መያዙን የከተማው አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ፅህፈት ቤት አስታወቀ።
የቤንዚን እጥረት የተከሰተ ለማስመሰል ህገወጥ በሆነ መንገድ የሚሰሩ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያቀፈ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደስራ መግባቱንም ከተማ አስተዳደሩ ገልጿል።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ሎቢሶ ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማዋ ሰሞኑን የቤንዚን እጥረት የተከሰተ ለማስመሰል የሚደረጉ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች ተስተውለዋል።
ይህን ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ ለመከላከል ግብረ ሀይል ተቋቁሞ የነዳጅ ማደያዎችን፣ በህገ-ወጥ ድርጊቱ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን መኖሪያ ቤት ድንገተኛ ፍተሻ የማድረግ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል ።
ኃላፊው እንዳሉት ከኅብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ ግብረ-ሀይሉ ትናንት 9:ሰዓት ንግድ ፈቃድ የሌላቸው ሁለት ግለሰቦች መኖሪያ ቤት ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ የተከማቸ ከ6 ሺህ 500 ሊትር በላይ ቤንዚን መያዝ ችሏል።
ግብረ-ሀይሉ ግለሰቦች መኖሪያ ቤት ድንገተኛ ፍተሻ ያደረገው በከተማዋ የቤንዚን እጥረት እንደተከሰተ በማስመሰል ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ ከሁለት ነዳጅ ማደያዎች ጋር በመመሳጠር ቤንዚኑን መደበቃቸው ከህብረሰተቡ በደረሰ ጥቆማ ነው ብለዋል።
ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ቤንዚን በመሸሸግ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ የሚሰሩ የነዳጅ ማደያዎችንና የግለሰቦችን መኖሪያ ቤቶች በመለየት የሚደረገው ድንገተኛ ፍተሻና ቁጥጥሩ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አስታውቀዋል።
ቤንዝኑን እንደደበቁ የተጠረጠሩት ግለሰቦች ለጊዜው የተሰወሩ ሲሆን፤ ከግለሰቦቹ ጋር በመመሳጠር በህገ-ወጥ ተግባሩ የተሳተፉ የሁለት ነዳጅ ማደያ ባለቤቶችን በህግ ጥላ ስር ለማዋል ከፀጥታ ሀይሎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የከተማው የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከይሩ አምዲኖ በበኩላቸው የአቅርቦት እጥረት እንደተከሰተ በማስመሰል ምርትን በመሸሸግ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ህገ-ወጥና የሚያስጠይቅ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
አስተዳደሩ በህገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ ተገቢና የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ግብረ ሃይል አቋቁሞ የመቆጣጠርና ክትትል የማድረግ ስራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
በተለይም በመንግሥት ድጋፍ የሚቀርቡ ምርቶችን በመሸሸግ በህብረተሰቡ ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የሚሰሩ አካላትን ለህግ ለማቅረብ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በህገ-ወጥ መንገድ የቤንዚን እጥረት እንዲከሰት የሚያደርጉ አካላት ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ስኬታማ እንዲሆን ህብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት የጀመረውን ትብብር እንዲያጠናክር አሳስበዋል።