ቀጥታ፡

የንግድ ባንኮች ዐቢይ ትኩረት ምን ይሁን?

የካቲት 11/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ ፋይናንስ ዘርፍ ተዋናይ የሆኑት ንግድ ባንኮች ዐቢይ ትኩረት ምን መሆን አለበት?

የአፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ እስራኤል ካሳ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ሰርተዋል።

በርካታ የሕብረት ስራ ማህበራትና የፋይናንስ ተቋማትን በማቋቋም የካበተ ልምድም ባለቤት ሲሆኑ በባህላዊ መረዳጃ ማህበራት፣ በምሁራንና የንግድ ዘርፍ ማህበራት የቦርድ አባልነትን ጨምሮ የነቃ ተሳትፎ ያደርጋሉ።

ኢትዮጵያን ለማሳደግ የፋይናንስና የትምህርት ዘርፎች ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው የሚሉት አቶ እስራኤል፤ መንግስት፣ ነጋዴው፣ የፋይናንስ ተቋማትና ተገልጋዩ ተቀናጅተውና ተናበው ሊራመዱ ይገባል ይላሉ።

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ንግድ ባንኮች በዋስትና ብድር ወይም በኮላተራል ስርዓት ብድር ከመንጠልጠል ይልቅ ተመጋጋቢ በሆነ አግባብ ከሀሳብና የገበያ ትስስር ማዕከል ያደረገ የባንክ ብድር አገልግሎት መዘርጋት እንዳለበትም ይናገራሉ።

በሌላ በኩል በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና እውን ለማድረግ እየተሰራ ባለበት ሁኔታ የኢትዮጵያ የንግድ ባንኮች ከሌሎች የአፍሪካ ባንኮች ጋር መተሳሰርና አፍሪካዊ የንግድ ትስስርን ማጠናከር አለባቸው ነው የሚሉት።

በአፍሪካ ባንኮች በአቅማቸው፣ በቅንጅታዊ አሰራራና በዲጂታል ስርዓት አተገባበራቸው ልቀው ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመው 'ንግድን የተቆጣጠረ አገር ሃያል ነው' ሲሉም አስረድተዋል።

በተለይም 80 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም የሚሆንበትን ኢትዮጵያዊነትና አፍሪካዊነት ስትራቴጂ ነድፎ በመስራት የመሪነቱን ሚና ሊጫወት ይገባል ነው ያሉት።

በአገሪቷ ከ80  በመቶ በላይ የሰው ሀይል በአነስተኛና መካከለኛ ኢንርተርፕራይዞች ላይ የተሰማራ መሆኑን ገልጸው፤ እነዚህን ኢኮኖሚ ዘርፎች ባንኮች መደገፍ ይገባቸዋል ሲሉም መክረዋል።

በመሬት አጠቃቀም ስርአቱ ሃብት እንዲባክን የሚያደርገውን አሰራር ማሻሻል እንዲሁም መንግስት የፋይናንሱን ዘርፍ ከመሬት ሀብት ጋር ማስተሳሰር እና ወጣቱን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስርዓት መዘርጋት አለበት ብለዋል።

በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች በልዩ ሁኔታ አተኩረው የሚንቀሳቀሱ የኢንቨስትመንት ባንክ፣ የግብርና ባንክ፣ የኢንዱስትሪ ባንክ፣ የኮንስትራክሽን ባንክ እንዲሁም የመሰረተ ልማት ባንኮች በተናጠል ሊቋቋሙ ይገባል የሚልም ሃሳብ አላቸው።

በተለያዩ አገራት የሰራተኛውን ኢኮኖሚዊ ችግር በመፍታት የሚታወቁት ሕብረት ስራ ባንኮችን ማቋቋም በተለይም ለቁጠባ ብድርና ባህል ዕድገት ለሰራተኛው ተጠቃሚነት ትልቅ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

ከ50 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የቆመው የባንኮች የስቶክ ወይም የአክሲዮን ገበያ ቢጀመር ዳያስፖራውና አርሶ አደሩ በቀላል ገንዘብ ተጠቃሚ እንደሚሆን ገልጸው፤ የስቶክ ወይም ሕጋዊ የገንዘብ ሰነድ መገበያያ ስርዓት ጉዳይ በፍጥነት ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል ይላሉ።

የአክሲዮን ገበያ ቢኖር ዜጎችን ወደ ባለሀብትነት ለማሳደግ፣ የልማት ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ለመገንባት እና ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር አይተኬ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በየባንኮች የተቀመጡ ገንዘቦች ለአብነትም የጡረታና ሌሎችም ወደ ኢንቨስትመንት የሚለወጡበትን አሰራር መፍጠርም ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ተቀማጭ ገንዘቦችን የመኖሪያ ቤት ልማትን ጨምሮ ሌሎች ኢንቨስትመንቶች ላይ ማዋል ተገቢ መሆኑን ያስረዳሉ።

ጠንካራ ንግድ ምክር ቤትና ሰራተኛ ማህበራት በማቋቋም ለወጣቶች ስራ ዕድል መፍጠር፣ ነዋሪውን የቤት ባለቤት ማድረግና ኑሮውን ማሻሻል በፋይናንስ ዘርፉ አቢይ ትኩረት ተደርጎ መቀየስ አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም