ከውጭ የሚገቡ የቆዳ ውጤቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የአምራች ኢንዱስትሪውን የማጠናከር ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከውጭ የሚገቡ የቆዳ ውጤቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የአምራች ኢንዱስትሪውን የማጠናከር ስራ እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ የካቲት 11/2014(ኢዜአ) ከውጭ የሚገቡ የቆዳ ውጤቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የአምራች ኢንዱስትሪውን በልዩ ሁኔታ የማጠናከር ስራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ኢትዮጵያ በእንስሳት ሃብቷ ከአፍሪካ ቀዳሚ ስትሆን ከዓለም አገራት ደግሞ ከሶስት አገራት መካከል ትጠቀሳለች።
ሆኖምያላትን ሃብት በአግባቡ ካለመጠቀም ጋር ተያይዞ እምብዛም ውጤታማ እንዳልሆነችና በርካታ የቆዳ ውጤቶችን ከውጭ እንደምታስገባ ይነገራል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የኮቪድ-19 ወረርሽንና ሌሎች ተግዳሮቶች ለቆዳና ሌጦ ኢንዱስትሪው ገበያ መቀዛቀዝ ምክንያት ያላትን ሃብት በአግባቡ ለመጠቀም ተጨማሪ ተግዳሮት ሆኗል።
የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ ከ90 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም እድገቱና እያስመዘገበ ያለው ውጤትም አነስተኛ መሆኑ ይነገራል።
ሆኖም የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የቆዳና ሌጦ ውጤቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሪ ለማዳን እየሰራ ይገኛል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዳኛቸው ሽፈራው በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ከውጭ የሚገባውን የቆዳ ውጤት በአገር ውስጥ ለመተካት የአምራች ኢንዱስትሪውን አቅምና ጥራት ለማሳደግ እየተሰራ ነው።
በኢትዮጵያ በህጋዊም ሆነ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ የቆዳ ምርት ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት የቆዳና ሌጦ ውጤቶች በአገር ውስጥ ገበያ በስፋት በማምረት የውጭ ምንዛሪ ለማዳን እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር ባለፉት ዓመታት በተከሰቱ የኮሮናና መሰል ችግሮች ሳቢያ የቆዳ ኢንዱስትሪው የገበያ ችግር ውስጥ ገብቶ መቆየቱን ጠቁመዋል።
ይህን ችግር ለማቃለል የተለያዩ ስራዎች እየተተገበሩ መሆኑን ጠቅሰው ከሚሰሩት ስራዎች መካከል የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅምንና ጥራትን ማሳደግ ዋነኛው ነው ብለዋል።
በአገር ውስጥ የተማሪዎችን፣የመከላከያ ሰራዊት ጫማዎችንና ቦርሳዎችን በስፋትና በጥራት ማቅረብ መጀመሩንም ነው አቶ ዳኛቸው የተናገሩት።
የውጭ ገበያው ውስጥ በብዛትም በጥራትም ለመግባት የሚያስችሉ ሁኔታዎች መፈጠራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ማህበር ተወካይና የሶልጌት ሌዘር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤት አቶ ሰለሞን ጌቱ፤ የቆዳና ሌጦ ኢንዱስትሪው ገጥመውት የነበረውን ተግዳሮቶች መንግስት በወሰዳቸው የመፍትሄ ርምጃዎች ውጤት መታየቱን ጠቅሰዋል።
የቆዳና ሌጦ የጥራት ችግር እንዲሁም የኮቪድ 19 ወረርሽኝና ሌሎች ተግዳሮቶች ለቆዳና ሌጦ ኢንዱስትሪው ገበያ መቀዛቀዝ ምክንያት መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡
የቆዳና ሌጦ ምርት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለአገሪቱ ጥሩ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እንደሚያመጣ ሴክተሩን በስልጠና፣ በፋይናንስና በተለያዩ ዘርፎች መደገፍ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ዘርፉን ለማጠናከርና ለመደገፍ የተጀመሩ አንዳንድ ስራዎች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ጌቱ ጅማሮው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የአገር ውስጥ ገበያ በስፋት መፈጠሩ ኢንዱስትሪዎቹን ወደ ስራ ከማስገባት ባለፈ ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባቸውን ምርቶች በመቀነስ ከወጪ ይታደጋል ብለዋል።