ቀጥታ፡

በአፍሪካ እና አውሮፓ ህብረት የጋራ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የአፍሪካን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን አከናውነዋል

የካቲት 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአፍሪካ እና አውሮፓ ህብረት የጋራ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የአፍሪካን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስኬታማ ተግባራት ማከናወናቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልገሎት አስታወቀ፡፡

የአውሮፓ ህብረትና የአፍሪካ ህብረት የጋራ ጉባኤ በቤልጂየም ብራሰልስ እየተካሄደ ሲሆን፤ በጉባኤው የሁለቱን ህብረቶች አባል አገራትን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ እየመከረ ነው፡፡

በጉባኤው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባኤው ላይ የአፍሪካን ብሎም የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት የሚያጠናክሩ ሃሳቦችን ያነሱ ሲሆን፤ ከዚህ ጎን ለጎንም የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ማኑኤል ማክሮንን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባኤው ባደረጉት ንግግር በተለይ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተጎዳውን የአፍሪካ ኢኮኖሚ መደገፍ እንደሚገባ አጽኖት መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡

ወረርሽኙ በአፍሪካ ካሳደረው ተጽእኖ አንጻር እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ አለመሆኑን አንስተው፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማስገንዘባቸውንም ሚኒስትር ዴኤታዋ በስፍራው ለሚገኘው የኢዜአ ሪፖርተር ተናግረዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ አካታች እድገት እንዲመጣ የፋይናንስ ትብብር ስራዎች አፍሪካን ማዕከል ያደረጉ እንዲሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአውሮፓ ህብረት በአፍሪካ መሰረተ ልማትን ለማጠናከር የሚከናወኑ ተግባራትን ለመደገፍ ቃል የገባውን የ150 ቢሊዮን ዩሮ ድጋፍ አድንቀው፤ ሌሎች የልማት ድጋፎችም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መጠየቃቸውንም ነው የገለጹት፡፡

ለአፍሪካ የሚደረጉ ድጋፎች አጀንዳ 2063 እና የዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካትን ማዕከል ያደረጉ ሊሆኑ እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስተሩ አንስተዋል።

ከዚህ አኳያ የአውሮፓ ህብረት በተለይ አፍሪካዊያንን ይበልጥ እርስ በርስ ለማስተሳሰር የሚደረጉ ጥረቶችን  እንዲደግፍ ጠይቀዋል ነው ያሉት፡፡ 

በቤልጂየም፣ ሉክሰንበርግና በአውሮፓ ተቋማት የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛና አምባሳደር ሂሩት ዘመነ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጉባኤው ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ፍሬያማ የሁለትዮሽ ውይይቶችን ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጓቸው የሁለትዮሸ ውይይቶች መንግስት በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን የሄደባቸው ርቀቶችን ማስገንዘባቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የገጠሟትን ችግሮች ተቋቁማ ለውጥ እያስመዘገበች ያለች አገር መሆኗን መናገራቸውንም ነው ያነሱት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ በመስኖ እና አረንጓዴ ልማት እንዲሁም በስራ ፈጠራ መስክ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን እንዳብራሩም አምባሳደር ሂሩት ተናግረዋል፡፡ 

በሁለቱ ህብረቶች የጋራ ድንጋጌ ላይ ኢትዮጵያ ያነሳቻቸው በርካታ ሃሳቦች መካተታቸውን ገልጸው፤ በአጠቃላይ በጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካን ብሎም የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን ስለማከናወበናቸው አውስተዋል፡፡ 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም