የጥጥ፣የግብርና ልማትና እንስሳት እርባታ ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ትኩረት ሊደረግ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የጥጥ፣የግብርና ልማትና እንስሳት እርባታ ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ትኩረት ሊደረግ ይገባል
የካቲት 10 ቀን 2014 (ኢዜአ)በጥጥ፣ በግብርና ልማትና በእንስሳት እርባታ ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾችና ሙያተኞች ጠየቁ።
የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢኒስቲትዩት ''ሶሊዳሪዳድ'' ከተሰኘ በጨርቃ ጨርቅ ፣ በቆዳ ፣ በቡና በከብት እርባታ ምርቶች ላይ ከሚሰራ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር በመተባበር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በውይይቱ በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾች ሙያተኞችና ተመራማሪዎች የጥጥ፣ የግብርና፣ የእንስሳት እርባታና መኖን ተረፈ ምርት መልሶ በመጠቀም ረገድ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ አንስተዋል።
በዚህም አምራቾቹም ሆነ አገሪቷ ከዘርፉ ማግኘት ያለባቸውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በአግባቡ እያገኙ ባለመሆኑ ጠቀሜታውን ለማሳደግ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በጥጥ ልማት የተሰማሩት አቶ ሃዱሽ ግርማይ፤ በኢትዮጵያ የጥጥ ልማትን በሃላፊነትና በባለቤትነት የሚያሰራና የሚመራ ቀጥተኛ አካል የለም ይላሉ።
እሳቸው በሚሰሩበት በአፋርና በደቡብ ኦሞ አካባቢዎች ሰፋፊ የጥጥ እርሻዎች ቢኖሩም ካለው የምርት ምጣኔ አኳያ ጠቀሜታው እምብዛም መሆኑን ጠቅሰዋል።
በጥጥ ልማት ከዋናው ምርት ከሚገኘው ጠቀሜታ ባሻገር የጥጥ ፍሬን ለዘይት ፣ከዘይት የሚገኘውን ተረፈ ምርት ደግሞ ለከብቶች መኖ መጠቀም እንደሚቻል በማስረዳት።
ዘርፉን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ድርጅት የሽመና ባለሙያው አቶ ቴዎድሮስ ዘሪሁን እንዳሉት ባህላዊ የሽመና ሙያን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመደገፍ በጥራትና በስፋት ተደራሽ ለማድረግ የተሰራው ስራ አጥጋቢ አይደለም፡፡
በቀላሉ በአገር ውስጥ መመረት የሚችሉትና የተለያዩ አልባሳትን ለመስራት የሚያግዙት ድርና ማግ ከውጭ እንዲገባ መደረጉ ዘርፉ እንዲዳከም መንገድ ከፍቷል ብለዋል፡፡
አልባሳት ለመስራት የሚያገለግሉ ሁሉንም አይነት ግብአቶች በአገር ውስጥ ለማምረት ዘመናዊ የምርት ሂደትን አገር ውስጥ መጀመር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከማግኘት በዘለለ ሀገሪቱ የምታፈሰውን የውጭ ምንዛሪ ወጪ ማስቀረት ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ላይ የተሰማራው የፍርኤል ኢትዮጵያ ፒኤልሲ ድርጅት ተወካይ አቶ ፋሲካ ስዩም ድርጅታቸው በዋናነት የጥጥና የሙዝ ምርትን ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ ለሚያመርተው ምርት አስፈላጊው ጥበቃ እየተደረገለት ባለመሆኑ በምርቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰበት እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
በዚህም ድርቅ ሲከሰት ለመቋቋሚያ የሚያግዝ የመኖ ዝግጅት ባለመከናወኑ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ በሚገመት ምርት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል፡፡
ይህን ለመከላከል የሚረዳ ቅንጅታዊ አሰራርን በማዳበር የሚደርሰውን ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ማስቀረት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
የሶሊዳሪዳድ ኢትዮጵያ ሃላፊ ዶክተር ዘሪሁን ደሳለኝ በበኩላቸው በአምራቾቹ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ምርቱ በሚመረትበት አካባቢ ተረፈ ምርቶቹን የሚያቀነባብር መሳሪያ ሊኖር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በተለይም ተረፈ ምርት ያላቸውና መልሰው ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ምርቶች ከመመረታቸው በፊት ጎን ለጎን ግብአቶችን ማሟላት የጎላ ጠቀሜታ እንዳለውም አክለዋል፡፡ሠ
የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢኒስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሰለ መኩሪያ እንዳሉት አምራቾቹ ያነሷቸው ጥያቄዎች ተገቢነት ያላቸውና መፍትሄን የሚሹ ናቸው።
በውይይቱ የተነሱ ሃሳቦችን በግብአትነት በመጠቀም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንሰራለንም ብለዋል።
የአሰራርና የፖሊሲ ማሻሻያ የሚፈልጉ ጉዳዮች ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥባቸው ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩም አስረድተዋል።