የሰብአዊ መብቶች መከበርና የፍትህ ተደራሽነትን ማሳደግ የሚያስችል አገር አቀፍ የሰብአዊ መብት ምርመራ ሊደረግ ነው

89

የካቲት 10/2014/ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች መከበርና የፍትህ ተደራሽነት ማሳደግን አላማው ያደረገ አገር አቀፍ የሰብአዊ መብት ምርመራ ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በነጻነት መብት ላይ ትኩረቱን ያደረገ አገር አቀፍ የሰብአዊ መብት ምርመራ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ አውደ ጥናት ዛሬ አካሂዷል።

የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ፕሮጀክቱ የሰብአዊ መብቶች መከበርና የፍትህ ተደራሽነትን ለማሳደግና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን ብቃት ለማጎልበት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

ምርመራው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው መሆኑን ጠቁመው ውስብስብ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ስልታዊ በሆነ መንገድ ለመመርመር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ የ15 ሚሊዮን ዮሮ ድጋፍ የሚከናወን መሆኑንም አስረድተዋል።

የወንጀል ፍትህ ስርአቱን ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊና ተጠያቂነት የሰፈነበት ማድረግ፣ በተለይ ለሴቶችና ህጻናት ፍትህ ተደራሽ የሚሆንበትን ሁኔታ ማጎልበት ከፕሮጀክቱ ዝርዝር አላማዎች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የሰብአዊ መብት ምርመራው ከዚህ አመት ጀምሮ የሚያካሂድ መሆኑን ገልጸው በተለይ ለህጻናትና ሴቶች ትኩረት በመስጠት የነጻነት መብታቸው ላይ የደረሰውን ጥሰት በማጣራት ለሚመለከተው አካል ምክረ ሃሳብ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ማጎልበት የፕሮጀክቱ ዋነኛ ግብ መሆኑ ተገልጿል።

በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ አውደ ጥናት ላይ ከፌደራልና ከክልል የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን  አስፈላጊነቱ ላይ ውይይት አድርገውበታል።

ፍትህ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች የፍትህና የሰብአዊ መብት ተቋማት የፕሮጀክቱ ተሳታፊዎች መሆናቸውም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም