የጀጎል ግንብን ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ የማስዋብ ስራ እየተካሄደ ነው

103

ሐረር የካቲት 10/2014(ኢዜአ) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የጀጎል ግንብ ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የማስዋብ ስራ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ባህል፣ ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

ጀጎልን ለጎብኚዎች ውብና ምቹ ማድረግ በዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ከማሳደግ አንጻር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በቢሮው የቋንቋ ዳይሬክተር አቶ ጃሚ መሀመድ ፤  በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የጀጎል ግንብ ከንጽህና ጋር በተያያዘ ለጉዳት እየተዳረገ መምጣቱን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም "ጀጎልን ጽዱ እና ውብ እናድርጋት"  በሚል መሪ ሀሰብ በጀጎል የሚገኙ አሚር ኑር እና አባድር ወረዳዎችን በማስተባበር እና የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር እየተሰራ  መሆኑን ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ ጀጎልን ለጎብኚዎች ምቹና የመስህብ ቦታ በማድረግ  ቅርሱን ለትውልድ ለማስተላለፍ በተለይ ወረዳዎቹ ህብረተሰቡን አሳምነው በባለቤትነት መንፈስ መንቀሳቀሳቸው ስራው በተፈለገው መንገድ እንዲከናወን እያስቻለ ነው።

በጀጎል ውስጥ ከህብረተሰቡ የቆሻሻ አወጋገድ ጋር በተያያዘ አሁንም ክፍተቶች እንደሚስተዋል ጠቁመው፤ ችግሩን ለመፍታት ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ባለፈ በትምህርት ቤቶች በክባባት አማካኝነት ትምህርት እየተሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል።

ቅርስን ከመጠበቅ፣ ከመንከባከብ እና ከማልማት አንጻር ቢሮው እቅድ አውጥቶ የንቅናቄ ስራዎችን መጀመሩንም አቶ ጃሚ ተናግረዋል።

"የተባበረ ክንድ አንድ ላይ ለውጥ ያመጣል በሚል እምነት ሁለቱ ወረዳዎች ከክልሉ ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመሆን ህብረተሰቡን በማስተባበር ጀጎልን የማስዋብ ሥራ እየሰራን እንገኛለን" ያሉት ደግሞ የአሚር ኑር ወረዳ የከተማ ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አሚር ረመዳን ናቸው።

የቅርስ ጥበቃን መሰረት በማድረግ እየተከናወነ ያለው ሥራ ውጤት እየታየበት በመሆኑ በተለይ ጀጎልን ጽዱና ምቹ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የአሚር ኑር እና  የአባድር ወረዳዎች ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት እንዳሉት፣ ጀጎልን በማስዋብ የነዋሪዎችንም ሆነ የጎብኚዎችን ቀልብ መሳብ ይቻላል።

አሁን የተጀመረው አካባቢውን ጽዱና ውብ የማድረግ ሥራ ቱሪስቶች በሐረሪ ክልል የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን እንዲጎበኙ የሚጋብዝ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ከደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻዎች አወጋገድ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲስተካከሉ ጠይቀዋል።

ጀጎልን ማሳመር ጥቅሙ የሁሉም መሆኑን የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ ህብረተሰቡ ተባብሮ ጀጎልን ወደ ቀድሞ ታሪካዊ ውበቱ ለመመለስ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተገነባ የሚነገርለት የጀጎል ግንብ  አምስት በሮች ያሉት ሲሆን በውስጡም ከሚገኙት ታሪካዊ ቅርሶች መካከል ረጅም እድሜ ያስቆጠሩ መስጊዶችና የፈረንሳዊው ጸሐፊ የአርተር ራንቡ መኖርያ ቤት ይጠቀሳሉ።

ሙዚየሞች፣ የሐረሪ ባህላዊ ቤቶች፣ የጅብ ምገባ ትርዒት ማሳያ ስፍራ እንዲሁም ሌሎች ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ጥንታዊ የመስህብ ስፍራዎች እንደሚገኙበትም ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም