ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የተጀመረው ፍቅር፣ ሰላምና መደመር የበለጠ እንዲጎለብት የበኩሌን አደርጋለሁ- ታማኝ በየነ

አዲስ አበባ  ነሃሴ 26/2010በኢትዮጵያ የተጀመረው የፍቅርና የሰላም የመደመር አየር የበለጠ እንዲጎለብት የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አርቲስትና የፖለቲካ ተሳታፊ ታማኝ በየነ ገለጸ። ኢትዮጵያዊነትን በማቀንቀን የሚታወቀውና ከ22 ዓመታት በላይ ኑሮውን በአሜሪካ አድርጎ የነበረው ታማኝ በየነ ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብቷል። ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስም የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዶክተር አምባቸው መኮንን፣ ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ አርቲስቶችና ታዋቂ ግለሰቦች እንዲሁም አድናቂዎቹ ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል። ታማኝ በየነ በዚህ ወቅት ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫም ከ22 ዓመታት በፊት ከአገሩ ሲወጣ ተገፍቶ ለስደት መዳረጉን በመግለጽ አሁን ግን ከረጅም ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ አገሩ ሲገባ በተደረገለት ደማቅ አቀባበል በእጅጉ መደሰቱን ገልጿል። አርቲስት ታማኝ በኢትዮጵያ የተጀመረው የፍቅርና የሰላም የመደመርና የይቅርታ ጉዞ እንዲጎለብት የበኩሉን ለማበርከት ያለውን ዝግጁነት ተናግሯል። "ከሀገሬ ስወጣ ከፍቶኝ ተገፍቼ ነው የወጣሁት። ስመለስ ግን ቂም ይዤ አይደለም የመጣሁት በአገራችን የተጀመረው የይቅርታ የፍቅር አየር የበለጠ እንዲነፍስ እንደ አንድ ዜጋ የእኔ አስተዋፆ ቦታ ቢያገኝልኝ ብዬ ነው።የመበቃቀል የመጠፋፋት መከራ በኢትዮጵያ እናቶች ላይ ያደረሰውን ታውቃላችሁ። እኔ በጣም እድለኛ ነኝ  እናቴ ይኸው እዚህ ድረስ መጥታ ተቀበለችኝ አባቴን ግን መቅበር አልቻልኩም። እንኳን እኔ ባለቤቴ እናቷን መቅበር አልቻለችም ትንሽ ቀድሞ ቢሆን ኖሮ ለውጡ አሷም እናቷን መቅበር ትችል ነበር።ወደፊት  ሌሎች እናቶች እንዲህ እንዳይሆኑ አገራችን የሰላም የፍቅር አገር እንድትሆን ሁላችንም ድርሻ አለብን።" የአርቲስትና የፖለቲካ ተሳታፊ ታማኝ በየነ ወላጅ እናት እማሆይ ማሚቴ በበኩላቸው ልጃቸው ከረጅም ዓመታት የውጪ ቆይታ ወደ አገሩ በመመለሱ የተሰማቸውን ልዩ ስሜት እንዲህ ገልፀዋል። "በጣም ደስ ብሎኛል ቃልም አጣሁቃሌንማ ለእግዚአብሄር ስጥቻለሁ ምን ቃል አለኝ።እኔንም እዚህ ላደረሰኝ እግዛቤር ይመስገን። "  ታማኝ የበርካታ ሙያዎች ባለቤት ሲሆን የመድረክ አስተዋዋቂ፣ ኮሜዲያን፣ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች እና ተወዛዋዥ እንዲሁም በበጎ አድራጎት ተግባር በአገር ውስጥም ይሁን በዲያስፖራው ዘንድ ከፍተኛ ዕውቅናን ያተረፈ ነው። በተለይ ግሎባል አሊያንስ በተሰኘው ተቋም በውጭ አገር በተለያዩ አጋጣሚዎች ለአደጋ የተጋለጡ ኢትዮጵያውያንን በመደገፍ ይታወቃል። ከኢትዮጵያ ጋር በፖለቲካ ምክንያት ተራርቆ ለነበረው ዲያስፖራ ተወካይ መሆኑ ስለታመነበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ "ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ" በሚል መርህ በሰሜን አሜሪካ ባደረጉት ጉዞ የግንቡን መፍረስ ያበሰሩት እርሱን በማቀፍ ነበር።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም