በደቡብ ክልል የኢፋድ የልማት ፕሮግራም የህብረተሰቡን ህይወት ለማሻሻል ሚናው ከፍተኛ ነው -አቶ ርስቱ ይርዳው

70

ሀዋሳ ፤ የካቲት 10/2014 (ኢዜአ) በግብርና ልማት ዓለም አቀፍ ፈንድ (ኢፋድ) ፕሮግራም በደቡብ ክልል የሚካሔዱ የልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ህይወት በማሻሻል ረገድ ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ገለጹ ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከኢፋድ ካንትሪ ዳይሬክተር ከማዊራ ቺትማ ጋር በልማት ዙሪያ በጽህፈት ቤታቸው በተወያዩበት ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ በኢፋድ ፕሮግራም የሚተገበሩ የልማት ስራዎች ለውጥ እያመጡ ነው።  

ፕሮግራሙ በገጠር ፋይናንስና በአርብቶ አደሩ ህይወት ማሻሻል ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል ።

የአነስተኛ መስኖ ልማት ስራዎችን ማጠናከር እንዲሁም አስፈላጊ የግብርና ግብአቶችን ማቅረብ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።  

ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በኢፋድ ፕሮግራም በክልሉ የሚካሔዱ የልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ህይወት በማሻሻል ረገድ ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም  ከአጋር ድርጅቶች ጋር የሚደረገውን የትብብር ስራ እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።

የመስኖ ልማት ስራውን ውጤታማ ለማድረግ የክልሉ መንግስት ከፍተኛ በጀት በመመደብ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ርስቱ ጠቁመዋል።

በቆላማ አካባቢዎች ተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋ እና ተያያዥ ችግሮች በአርብቶ አደሩ ህይወት ላይ ያስከተለው ጉዳት ከፍተኛ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤  ችግሮቹን ለማቃለል  በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል።

 የግብርና ልማት ዓለም አቀፍ ፈንድ (ኢፋድ) ካንትሪ ዳይሬክተር ማዊራ ቺትማ በበኩላቸው፤ በክልሉ እየታየ ያለው ሰላምና ጸጥታ አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንደደረሰ መመልከት እንደቻሉ ተናግረዋል።

በተለይ አነስተኛ መስኖ ልማት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ያለውን ፋይዳ በመግለጽ በአርሶና አርብቶ አደሩ ህይወት ላይ ለውጥ ማምጣቱንም  ጠቅሰዋል።

የክልሉ መንግስት የአነስተኛ መስኖ ልማት ስራ ስኬታማ ለማድረግ እየሰራ ያለው መልካም  መሆኑን ጠቁመዋል።

የህብረተሰቡን ህይወት ለመቀየር በሚካሔዱ ልማቶች ላይ በትብብር ለመስራት መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም