ቀጥታ፡

በወታደራዊ ቀላል አውሮፕላን መከስከስ ህይወታቸውን ያጡ የሰራዊት አባላትና ቤተሰቦች የቀብር ስነ ስርዓት ተፈፀመ

አዲስ አበባ ነሃሴ 26/2010 ከድሬዳዋ ወደ ቢሾፍቱ በበረራ ላይ በነበረው ንብረትነቱ የመከላከያ ሰራዊት የሆነ Dash 6 ቀላል የትራንስፖርት አውሮፕላን ላይ በደረሰ ድንገተኛ አደጋ ህይወታቸው ያለፈው የሰራዊት አባላትና የሠራዊት ቤተሰቦች የቀብር ስነ ስርዓት ትናንት ተፈፀመ። የቀብር ስነ ስርዓቱ በቢሾፍቱ በተፈፀመበት ወቅት የጦር ሀይሎች  ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮነንን ጨምሮ ከተለያዩ የሰራዊቱ ክፍል ጄኔራል መኮንኖች፣ የሟች ቤተሰቦች እንዲሁም የቢሾፍቱ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል። በአደጋው ህይወታቸው ያለፉትን ማንነት በመለየት ቤተሰቦቻቸው በፍጥነት ከያሉበት እንዲመጡ በማድረግ በቀብር ስነስርዓቱ ላይ እንዲገኙ መደረጉን የኢፌዴሪ አየር ኃይል ምክትል አዛዥ የሰው ኃይል ብርጋዴር ጄኔራል አስፋ ማመጫ ገልፀዋል። በአደጋው ህይወታቸው ያለፈው የሰራዊት አባላትና የሠራዊቱ ቤተሰቦች በየኃይማኖታቸው በክብር የቀብር ስነስርዓት መፈፀሙን ነው የተናገሩት። የቀብር ስነ ስርዓቱ በወታደራዊ ስነ ስርዓት ከተፈፀመ በኋላ በኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ስም የአበባ ጉንጉን የማስቀመጥ ስነ ስርዓት መካሄዱን ብርጋዴር ጄኔራል አስፋ ተናግረዋል። በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሟች ቤተሰቦች ለተሰዉት በተደረገው ደማቅ የቀብር ስነስርዓት ክብር እንደተሰማቸው ተናግረዋል። የሟች ቤተሰብ የሆኑት አቶ ደረጀ ደምሴ እንደተናገሩት፤ የቀብር ስነስርዓቱ ሂደትና መከላከያ የሰጠውን ክብር አድንቀዋል። ዳሽ ሲክስ የተባለው አውሮፕላን ከድሬዳዋ ወደ ቢሾፍቱ 17 ሰዎችን አሳፍሮ ነሐሴ 24 ቀን 2010 ዓም በመብረር ላይ እንዳለ ምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ ናናዋ ቀበሌ አካባቢ በመከስከሱ በውስጡ የነበሩ ሰዎች በሙሉ ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም