የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በቦረና ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ግማሽ ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በቦረና ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ግማሽ ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ
የካቲት 8/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በቦረና ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ግማሽ ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉን የአካባቢው ነዋሪና የህዝብ ወኪል በመሆን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ወይዘሮ ቲያ ሞዩ ተረክበዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሀፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው የድርቅ አደጋ በሰዎች ላይ መጠነ ሰፊ ችግር ተከስቷል ብለዋል።
በመሆኑም በችግር ጊዜ ደራሽ በመሆን የሰዎችን ህይወት ለመታደግ ሁላችንም የሚቻለነን ድጋፍ ማድረግ አለብን ብለዋል።
በዚህም የጉባኤው አባላት ከሆኑት ከሰባቱም ቤተ እምነቶች የተሰባሰበ ግማሽ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።
አካባቢው ከተከሰተው ከባድ ድርቅ አኳያ ድጋፉ በቂ ነው ባይባልም ሁላችንም ከተባበርንና ድጋፍ ካደረግን ችግሩን ማቃለል ስለሚቻል ለቸግር ደራሽ እንሁን በማለት ጥሪ አቅርበዋል።