ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል የሙርሌ ታጣቂዎች እያደረሱት ያለውን ጉዳት ለመከላከል እየተሰራ ነው

ጋምቤላ፤የካቲት 7/2014 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የሙርሌ ታጣቂዎች እያደረሱት ያለውን ድንበር ዘለል ጉዳት ለመከላከል አስፈላጊውን የጸጥታ ስምሪት በማደረግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።
የሙርሌ ታጣቂዎች  ከጥር 2014 ዓ.ም መግቢያ ጀምሮ እስካሁን ባደረሱት ጥቃት የ15 ሰዎች ህይወት ማለፉንና ስምንት ህፃናት ደግሞ ታፍነው መወሰዳቸው ተመልክቷል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኡቶው ኡኮት ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ ከደቡብ ሱዳን የሚመጡት የሙርሌ ድንበር ዘለል ታጣቂዎች በክልሉ እያደረሱ ያለውን ጥቃት ለማስቆም በየደረጃው የሚገኙ የጸጥታ አካላትን በማደራጀትና በማጠናከር በየስጋት ቀጠናዎች ስምሪት ተደርጓል።

ክልሉ ሰፊ የድንበር ወሰን ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ታጣቂዎቹ በተለይም በአኝዋና በኑዌር ዞኖች በሚገኙ ስምንት ጠረፋማ ወረዳዎች ተደጋጋሚ የጥቃት ሙከራዎች እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በእነዚሀ ሁለት  ዞኖች ከጥር  መግቢያ እስከ የካቲት 5/2014ዓ.ም. ባደረሱት ጥቃት  የ15 ሰዎች ህይወት ማለፉንና ስምንት ህፃናት ደግሞ ታፍነው መወሰዳቸውን አመልክተዋል።

እንዲሁም በሰባት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን ጠቁመው፤ ከአንድ መቶ በላይ የቀንድ ከብቶች መዝረፋቸውን ገልጸዋል።

የክልሉ ጸጥታ አካላት ታጣቂዎቹ እያደረሱ ያለውን ጥቃት ለማስቆም የሚሊሻ፣ የፖሊስና የልዩ ኃይል ፖሊስ ከፌዴራል የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በየስጋት ቀጠናው ተሰማርተው እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በጸጥታ አካላት ከሚደረገው የመከላከል ስራ ጎን ለጎን የክልሉ መንግስት ከፌዴራል መንግስት ጋር በመሆን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር ውይይት እየተደረገ ስለመሆኑም የቢሮው ምክትል  ኃላፊው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም