የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን በኦሮሚያ ክልል 12 ትምህርት ቤቶችን ልትገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን በኦሮሚያ ክልል 12 ትምህርት ቤቶችን ልትገነባ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 07/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን የ12 ትምህርት ቤቶችን ግንባታ ፕሮጀክቶች ገቢራዊ ለማድረግ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር ስምምነት ተፈራረመች።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል እና በኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አብዱልሀኪም ሙሉ፤ ስምምነቱን ተፈራርመዋል።
ቤተ ክርስትያኗ የምታስገነባቸው 12 ትምህርት ቤቶች ከቅድመ መደበኛ እስከ መሰናዶ የትምህርት ደረጃ ያላቸው እና 18 ሺህ ተማሪዎችን ለማስተናገድ አቅም የሚኖራቸው እንደሚሆኑ ተገልጿል።
ግንባታቸውም በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት የሚበቃ ሲሆን በምስራቅ ሸዋ፣ በሰሜን ሸዋና በፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞኖች ግንባታቸው ከሚካሄድባቸው ዞኖች መካከል እንደሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል፤ ቤተ-ክርስቲያኗ በማህበራዊ አገልግሎት በተለይም በትምህርት ሽፋን በየክልሉ ተደራሽ መሆኗን ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ገቢራዊ የሚደረጉት የትምህርት ቤት ግንባታ ፕሮጀክቶችም በዘርፉ የነበራትን ማህበራዊ አገልግሎት ለማስፋትና ከክልሉ መንግስት ጋር ይበልጥ ተባብሮ ለመስራት ያስችላል ብለዋል።።
የክልሉ መንግስት የፕሮጀክቶቹን ሃሳብ ተቀብሎ ስምምነቱ እንዲከወን ላደረገው ትብብር ምስጋና ችረዋል።
በኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አብዱልሃኪም ሙሉ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ማህበራዊ አገልግሎቶችን በስፋት እየተወጣች መሆኗን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ትምህርት ዘርፍ ጥራትና ሽፋን ረገድ ሰፊ ልምድ እንዳላት ጠቅሰው፤ አሁን ለመገንባት ያቀደቻቸው ትምህርት ቤቶችም በዚህ ረገድ ሚናቸው የጎላ እንደሚሆን ገልጸዋል።
የትምህርት ቤቶቹ መገንባት በትምህርት ተደራሽነት፣ በትምህርት ጥራት፣ በአገር ወዳድና የፈጠራ ባለቤት የሆነ ትውልድ ለማፍራት የላቀ ሚና እንደሚኖራቸው ነው ያነሱት።
የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቶላ በሬሳ፤ ቤተ-ክርስቲያኗ ለትምህርት ጥራት መሰረት የሆነችና በርካታ ብቁ ዜጎችን ያፈራች መሆኗን አውስተዋል።
ከቅድመ መደበኛ እስከ መሰናዶ ወይም 12ኛ ክፍል ደረጃ ያላቸው 12 ትምህርት ቤቶችን ግንባታም 18 ሺህ ተማሪዎችን ከማስተናገዳቸው ባሻገር ለ3 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጠር ገልጸዋል።
የመማር ማስተማር ሂደቱም በቅርቡ የተጀመረውን የገዳ ስርዓት የትምህርት አይነት እንደሚያካትት ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት ለትምህርት ቤቶቹ ግንባታ የሚሆኑ ቦታዎችን ከማቅረብ በተጨማሪ ግንባታቸው እንዲፋጠን ይከታተላል ብለዋል።