ከመንግስት የተሰጠን ወቅታዊ መረጃና ማብራሪያ ስለ ኢትዮጵያ እውነታ በቂ ግንዛቤ ፈጥሮልናል

አዲስ አበባ የካቲት 7/2014 /ኢዜአ/ ከመንግስት የተሰጠን ወቅታዊ መረጃና ማብራሪያ ስለ ኢትዮጵያ እውነታ በቂ ግንዛቤ ፈጥሮልናል ሲሉ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ አገራት ወታደራዊ አታሼዎች ተናገሩ።

በአዲስ አበባ ተቀማጭነታቸውን ላደረጉ የተለያዩ አገራት ወታደራዊ አታሼዎች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የመከላከያ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የውይይቱ ተሳታፊ ወታደራዊ አታሼዎች ስለ ኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ ትክክለኛውን መረጃ እንዲያውቁ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያ፣ በሱዳን፣ በኬንያና በጂቡቲ የስዊድን ወታደራዊ አታሼ ፓትሪክ ኤደንቶፍት ኢትዮጵያ ከጥቂት ወራት በፊት ከነበረችበት ስጋት መውጣቷንና መንግስት ችግሮችን በሰላማዊ ሁኔታ ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን በአግባቡ ተገንዝበናል ብለዋል።

መንግስት አገራዊ ችግሮችን በዘላዊነት ለመፍታት የጀመራቸውን ሰላማዊ እርምጃዎችም አድንቀዋል።

የአውስትራሊያ ወታደራዊ አታሼ አንድሬው ጊልበርት በበኩላቸው ወታደራዊ አታሼዎች መንግስት በየጊዜው የሚሰጣቸው ማብራሪያ ሀሰተኛውን እና እውነተኛውን ለመለየት ያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል።

በህወሃት በኩል የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች በርካቶችን እያሳሳቱ መሆኑን ጠቅሰው የመንግስት መረጃ ትክክለኛውን ነገር ለማወቅ አግዟል ብለዋል።

የመንግስት ማብራሪያ ለዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ትክክለኛው መረጃ ለማድረስ ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።

ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ ወታደራዊ አታሼዎች ማህበር ሊቀመንበር እና የናይጄሪያ ወታደራዊ አታሼ ኮሎኔል ኤሜካ አካሊሮ፤ በተመሳሳይ በተሰጣቸው ማብራሪያ እውንታውን እንደተረዱ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ጉዳይ በአንዳንድ ምዕራባውያን ሚዲያዎች ሲሰራጩ የነበሩ ሀሰተኛ መረጃዎች እውነታውን ሸፍነውት መቆየቱን አስታውሰው አሁን ላይ ትክክለኛውን ነገር ተረድተናል ብለዋል።

የአውስትራሊያ ወታደራዊ አታሼ አንድሬው ጊልበርትም የናይጄሪያውን አታሼ ሃሳብ በማጠናከር የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አገሪቷን የታደገበትና ያረጋጋበትን መንገድ አድንቀዋል።

ከጥቂት ወራት በፊት ስጋት ውስጥ የነበሩ አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት አስተማማኝ ደህንነት ስላላቸው ለመዘዋወር ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት አገራዊ ችግሮችን በዘላዊነት ለመፍታት ጥረቶች መጀመሩን አድንቀው፤ ለቀጣዩ አገራዊ ምክክር ፍሬያማነትም ተስፋቸውን ገልጸዋል።

ወታደራዊ አታሸዎቹ የወከሏቸው አገራት ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራቸው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ትብብርና አጋርነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም