በዞኑ በፀጥታ ችግር ምክንያት ሸሽተው የነበሩ ከ10 ሺህ በላይ የጉሙዝ ማህበረሰብ አባላት ወደ ቀያቸው ተመለሱ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በፀጥታ ችግር ምክንያት ሸሽተው የነበሩ ከ10 ሺህ በላይ የጉሙዝ ማህበረሰብ አባላት ወደ ቀያቸው ተመለሱ
አሶሳ፣ የካቲት 07/2014 ዓ.ም (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በፀጥታ ችግር ምክንያት ሸሽተው የነበሩ ከ10 ሺህ በላይ የጉሙዝ ማህበረሰብ አባላት የአካባቢያቸው ሰላም በመስፈኑ ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አስታወቁ።
ዋና አስተዳዳሪው አቶ ጋሹ ዱጋዝ እንደገለጹት እነዚህ ወገኖች ወደ ቀያቸው የተመለሱት የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የፌደራል ፖሊስን ጨምሮ የፀጥታ ኃይሎች ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት በሰሩት ስራ የአካባቢው ሰላም በመመለሱ ነው።
የመተከልን ሠላም ለመመለስ የቻለው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የክልሉ ልዩ ኃይል፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር በቅንጅት በመስራታቸው ነው ብለዋል።
እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ የፀጥታ ኃይሉ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ተቀናጅቶ በሰራው ስራ በአሁኑ ወቅት የዞኑ ሰላምና ፀጥታ እየተረጋጋ መጥቷል።
የአካባቢው መረጋጋትን ተከትሎ ለህይወታቸው ሰግተው ወደ ጫካ ሸሽተው የነበሩት የጉሙዝ ማህበረሰብ አባላት ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት ወደቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉን ገልጸዋል።
አብዛኞቹ ከማንዱራና ዳንጉር ወረዳዎች ሸሽተው የሄዱ እንደነበር ገልጸው፣ ያልተመለሱት እንዲመለሱ የፀጥታ ኃይሎች የተቀናጀ ጥረት እያደረጉ ነው ብለዋል።
በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን መስጠት ያልፈለጉ ቀሪ የታጣቂውን ቡድን አባላት የማያዳግም እርምጃ የመውሰዱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አቶ ጋሹ አስታውቀዋል።
በዞኑ የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ የጥፋት ቡድን በአሁኑ ወቅት ከህዝብ እየተነጠለና አቅሙም በከፍተኛ ሁኔታ እየተዳከመ መምጣቱንም ገልጸዋል።
በፀጥታ ችግር ምክንያት ተፈናቅለው በዞኑ በአራት ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ወገኖችም ሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው አመልክተዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን የመልሶ ማቋቋም እና አደጋ ምላሽ ዳይሬክተር አቶ አስረሳኸኝ አበጀ በበኩላቸው፣ ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፎችን ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ዳይሬክተሩ አያይዘውም ተፈናቃዮችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም የረጅም ጊዜ ስትራቴጂክ ዕቅድ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።
"ስትራቴጂክ ዕቅዱ በቀጣይ አምስት ዓመታት የሚተገበር ሲሆን ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋል" ብለዋል፡፡
ይኸው በጀት የወደሙ መኖሪያ ቤቶችን መልሶ መገንባትን ጨምሮ የውሃ፣ የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት እንደሚውልም አስረድተዋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት ዓመታት በጥፋት ቡድኖች በተከሰተ የፀጥታ ችግር ሳቢያ ከ345 ሺህ በላይ ወገኖች ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያዎች እንደሚገኙ ከኮሚሽኑ የተገኘ መረጃ ያሳያል።