ቀጥታ፡

አርቲስት ታማኝ በየነ አዲስ አበባ ገባ

አዲስ አበባ ነሃሴ 26/2010 ለረጅም አመታት በውጭ አገር ትግል ሲያደርግ የቆየው አክቲቪስትና አርቲስት ታማኝ በየነ ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብቷል:: አርቲስቱ ቦሌ አለም ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዶክተር አምባቸው መኮንን እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውለታል፡፡ እንዲሁም የአርቲስቱ አድናቂዎች፣ ወዳጅ ዘመዶችና የኪነጥበብ ባለሙያዎች በአቀባበሉ ላይ ተገኝተዋል፡፡ አርቲስት ታማኝ በቦሌ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ወደኢትዮጵያ በመምጣቱ የተሰማውን ደስታ ገልጿል፡፡ ከሚወዳት አገሩ ተገፍቶ ወጥቶ በፍቅር መመለስ መቻሉ የተለየ ስሜት የፈጠረለት እንደሆነም ተናግሯል፡፡ የነበረው የበቀልና የክፋት ፖለቲካ በብዙዎች ላይ በተለይም በኢትዮጵያውያን እናቶች ላይ ያደረሰው ጉዳት ከባድ እንደነበረ አስታውሷል፡፡ በአገሪቱ በመጣው ለውጥ ወደአገሩ በመግባት ወላጅ እናቱን በህይወት ለማግኘት በመቻሉ እድለኛነቱን  ገልጾ የትዳር አጋሩ አርቲስት ፋንትሽ በቀለ ከወራት በፊት በሞት የተለዩአትን እናቷን ለመቅበር አለመቻሏ የሚያስቆጭ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ የጥበብ ሰው የሰብአዊ መብት ተሟጋችና ንቁ የፖለቲካ ተሳታፊው ታማኝ በየነ ጐንደር ውስጥ አይከል በተባለው ከተማ በ1955 ዓ.ም. ተወለደ። ታማኝ ከልጅነቱ አንስቶ በቲያትርና በሙዚቃ ክበባት ውስጥ በድምፃዊነት ያገለግል ነበር፡፡ በ1969 ዓ.ም. ጋይንት አውራጃ ውስጥ በግል ጥረቱ ባቋቋመው የህፃናት የኪነት ቡድን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የአስተዋዋቂነት ሚና በመውሰድ ከተጫወተ በኋላ  የክፍለሀገሩ የኪነት ቡድን አስተዋዋቂ ሆኖ እንዲሰራ ዕድል አገኘ። ታማኝ በ1974 ዓ.ም. ለቀይ ኮከብ ዘመቻ ከብሄራዊ ቲያትር ተጨዋቾች ጋር ወደ አሥመራ በመሄድ ከሌሎች ከያኒያን ጋር ከመተዋወቁም በላይ የተዋጣለት ዝግጅት ለማቅረብ በቅቷል። ሚያዚያ 30 ቀን 1975 ዓ.ም. ለትንሣኤ በዓል ዋዜማ በተዘጋጀው የሙዚቃ ድግስ ላይ  በብሄራዊ ቲያትር ቤት የነበረውን ተመልካች ሲያስጨበጭብ ፕሮግራሙ በቀጥታ በቴሌቪዥን ይተላለፍ ስለነበር በዚህ ቀን ከመላው የኢትዮጵያ ተመልካች ጋር የመተዋወቅ እድል አጋጠመው፡፡ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ በኋላ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደ ዝግጅት ላይ ባደረገው ንግግር ምክንያት እስር ቤት ገባ፡፡ ከእስር ከወጣ በኋላም በአገር ያለነጻነት ከመኖር በስደት በነጻነት መኖር ይሻላል በሚል ከሚወዳት ሀገሩ ተለይቶ ቆይቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአሜሪካ ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በዋሽንግትን ዲሲ በነበራቸው ቆይታ ”ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ“ በሚል መሪ ሃሳብ በተዘጋጀው መድረክ ላይ ከአርቲስት ታማኝ ጋር በመተቃቀፍ የጥላቻ ግንብ መፍረስ መጀመሩን ማብሰራቸው ይታወሳል ፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም