በአገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ምዘና ውድድር የስነ ምግባር ጉድለት የታየባቸው ስፖርተኞች ተቀጡ - ኢዜአ አማርኛ
በአገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ምዘና ውድድር የስነ ምግባር ጉድለት የታየባቸው ስፖርተኞች ተቀጡ
አዲስ አበባ ነሀሴ 25/2010 በስድስተኛው አገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች የምዘና ውድድር በመሳተፍ ላይ ያለው የሐረሪ ክልል የወንዶች እግር ኳስ ቡድን በፈጸመው የስነ ምግባር ጉድለት ተቀጣ። ቡድኑ ቅጣት የተጣለበት በትናንትናው ዕለት የሐረሪ ክልል ከአማራ ክልል ጋር ለፍፃሜ ለማለፍ ባደረጉት ጨዋታ የሐረሪ ክልል እግር ኳስ ቡድን በስነ ምግባር ጉድለት የተቀጣ ተጨዋችን በማሰለፉ ነው። ዊልያም ሰለሞን የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በ2010 ዓ.ም የሚሰጠውን ስልጠና በመከታተል ላይ ሳለ በፈጸመው በስነ ምግባር ጉድለት መሰናበቱ ይታወቃል። ሁለቱ ቡድኖች በመደበኛው የጨዋታ ጊዜ 1ለ1 ተለያይተው በመለያ ምት ሐረሪ አማራን 4 ለ 2 ያሸነፈ ቢሆንም የሐረሪ ክልል ያሰለፈው ተጨዋች በስነ ምግባር የተቀጣ በመሆኑ የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ ጨዋታው እንዲሰረዝ አድርጓል። በመሆኑም የአማራ ክልል እግር ኳስ ቡድን 3-0 በፎርፌ አሸናፊ እንዲሆንና 3 ነጥብና 3 ተጨማሪ ጎል ተመዝግቦለታል። የሐረሪ ክልል የወንዶች እግር ኳስ ቡድን ያሰለፈው ዊልያም ሰለሞን ለአንድ ዓመት፣ የቡድኑ አሰልጣኝ አቶ እስክንድር ወልደማሪያምና የቡድኑ መሪ ኑረዲን ሲራጅ ተገቢ ያልሆነ ተጫዋች ሆን ብለው በማሰለፋቸው ከሙያቸው ለስድስት ወር እንዲታገዱ ተደርጓል። በዚሁ መሠረት ኦሮሚያ ከአማራ እሁድ 8:00 ሰዓት ለፍፃሜ የሚጫወቱ ሲሆን ደቡብ ከሐረሪ ለደረጃ ይጫወታሉ። በሌላ በኩል በሴቶች እግር ኳስ ደግሞ ደቡብ ከአዲስ አበባ ለፍፃሜ የሚጫወቱ ሲሆን ኦሮሚያ ከሐረሪ ለደረጃ ይጫወታሉ፡፡ በውኃ ዋና የምዘና ውድድር የአማራ ክልልን ወክላ የተወዳደረችው ሜሮን አበራ በ2006 ዓ.ም በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ስልጠና መውሰዷ እየታወቀ ክልሉ በማሰለፉ በእሷ አሸናፊነት የተገኘ 7 ወርቅ፡ 4 ብር እና 2 ነሐስ ሜዳሊያ እንዲነጠቅ ተደርጓል። በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደው የውኃ ዋና ውድድር አማራ በ15 ወርቅ፣ 14 ብርና በ7 ነሐስ አንደኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ኦሮሚያ 14 ወርቅ፣ 14 ብርና በ11 ነሐስ በማግኘት በሁለተኛነት ውድድሩን አጠናቋል። እንዲሁም ደቡብ በ9 ወርቅ፣ በ11ብርና በ8 ነሐስ የሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ፈጽሟል። የታዳጊ ወጣቶች የምዘና ውድድር በኦሮሚያ ክልል ከነሐሴ 13 ጀምሮ በ17 የስፖርት ዓይነቶች ከ2 ሺህ በላይ ስፖርተኞች በአዳማ፣ በአሰላና በቢሾፍቱ እየተካሄደ ሲሆን በመጪው እሁድ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የላከው መግለጫ ያመለክታል።