የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ በኳታር ከሚገኙ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላትና የሐይማኖት አባቶች ጋር ተወያየ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ በኳታር ከሚገኙ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላትና የሐይማኖት አባቶች ጋር ተወያየ
የካቲት 7 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ በኳታር ዶሃ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላትና የሐይማኖት አባቶች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ተወያየ።
የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ኑሯቸውን በኳታር ካደረጉ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የሃይማኖት ተቋማት አባቶች ጋር መወያየታቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በውይይቱም ጉባኤው በኳታር ዶሃ ወደፊት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ስለሚከፍትበት ሁኔታ ምክክር መካሄዱን አመልክተዋል።
“በኳታር የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ከእምነት ተቋማት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ሰብአዊ ድጋፍ ስለሚያደርጉበት እንዲሁም ድርቅ ባጋጠማቸው አካባቢዎች ሕብረተሰቡን ስለሚያግዙበት ሁኔታ ተነስቷል” ብለዋል።
“በሌላ በኩል አንዳንድ አካላት የወቅቱን አገራዊ ሁኔታ እንደጥሩ አጋጣሚ በመውሰድ በሃይማኖቶች መካከል የፖለቲካ እና ሌሎች ልዩነቶችን በመፍጠር የሚያካሂዱትን ተግባር በተመለከተ ሰፊ ምክክር ተደርጓል” ሲሉ ተናግረዋል።
በኳታር ዶሃ የጋራ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ አደራጅ ኮሚቴ በመሰየምም ከግንቦት 18 ቀን 2014 ዓ.ም በኋላ ቅርንጫፍ ጽ/ ቤቱ በይፋ እንደሚመሠረት መወሰኑን ጠቅላይ ጸሐፊው ገልጸዋል።