ቀጥታ፡

የፍትህ ሥርዓቱን ለማጠናከር የሚያስችሉ የአሰራርና አደረጃጀት ማሻሻያዎች እየተደረጉ ነው

የካቲት 6/2014/ኢዜአ/ የፍትህ ሥርዓቱን ለማጠናከር የሚያስችሉ የአሰራርና አደረጃጀት ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ ገለጹ።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 'የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አሁናዊ ሁኔታ'' በሚል መሪ ኃሳብ ዓመታዊ ጉባኤውን አካሂዷል።

በጉባኤው ከ2013 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ የተከናወኑ ተግባራትን የሚዳስስ ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፤ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድም ይፋ ሆኗል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት አሰጣጥ ለማቀላጠፍ የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎች ተደርገዋል።

ማሻሻያዎቹ በተለይም በዳኞች ነጻነት፣ ገለልተኝነትና ተጠያቂነት፤ በአገልግሎት ጥራት፣ ቅልጥፍና እና  ተደራሽነት እንዲሁም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማስረጽ ላይ ትኩረት ያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘርፉ የተመዘገቡ ለውጦችን ይበልጥ ለማጠናከር በቀጣይ ተጨማሪ የአሰራር ማሻሻያዎች እንደሚደረጉም  ጠቁመዋል።

በተለይም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይጸድቃሉ ተብለው የሚጠበቁ መመሪያዎች የፍርድ ቤቶችን አሰራር በማሻሻል ረገድ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የአሰራር ማሻሻያዎቹን ተከትሎ አዲስ አደረጃጀት ማዋቀርና የነበሩትን ደግሞ የማሻሻል ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

በጉባኤው ስትራቴጅክ እቅዱን ይዘት የሚዳስስ ጽሁፍ ያቀረቡት የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተስፋይ ነዋይ፤ እቅዱ በዘርፉ መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

እቅዱ ስምንት ዋና ዋና ጉዳዮችን የያዘ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይ ቀልጣፋና ፍትሃዊ አሰራርን ለመዘርጋት ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እቅዱ ዳኞች ነጻነታቸው ሳይጓደል እንዲሰሩና ለሚያጠፉት ጥፋትም ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራርን የያዘ መሆኑንም አብራርተዋል።

በጉባኤው የክልል ፍርድ ቤት ዳኞች የፌዴራልና የአዲስ አበባ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የኃይማኖት አባቶችና የረድኤት ተቋማት ተወካዮች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም