የድሬዳዋ ፖሊስ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት በአርአያነት የሚጠቀስ ነው- ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋ ፖሊስ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት በአርአያነት የሚጠቀስ ነው- ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
ድሬዳዋ፤ የካቲት 5/2014(ኢዜአ) የድሬዳዋ ፖሊስ ህብረተሰቡንና ባለሃብቱን በማስተባበር እያከናወናቸው የሚገኙት የሰላምና ህግ የማስከበር ተግባራት ለሌሎች አካባቢዎች በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ተናገሩ።
የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን የ595 አመራሮችና አባላት የማዕረግ ዕድገት የሰጠ ሲሆን ያስገነባቸው ፕሮጀክቶችም አስመርቋል፡፡
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ኮሚሽነር ጀነራሉ እንደተናገሩት፤ በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ የፖሊስ ተቋማት ሥርነቀል ለውጥ በማምጣት አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል፡፡
የዚሁ ለውጥ አካል የሆነው የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን ከፌደራልና ከተጎራባች ክልሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር በድሬዳዋና በምስራቅ አካባቢ ሰላምና ፀጥታ በማስፈን በአርአያነት የሚጠቀስ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡
በየደረጃው የሚገኘውን ህብረተሰብንና ባለሃብቱን ከጎኑ በማሰለፍ ከሶስት ዓመታት በፊት በድሬዳዋ ተከስቶ የነበረውን የፀጥታ ችግር እንዲወገድ በማድረግ ያመጣቸው ውጤቶች በመልካም ተሞክሮን በመውሰድ ለሌሎች አካባቢዎች መማሪያ እንዲሆኑ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
ዛሬ የተመረቁት ፕሮጀክቶች የዚሁ የተቀናጀ ውጤት አንዱ ማሳያ ነው፡፡
በቀጣይም ይህ ፍሬያማ ሂደት ለሌሎች ሀገራት ጭምር ምሳሌ በሚሆን መንገድ መሰራት እንዳለበት አመልክተው፤ የፌደራል ፖሊስም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፤ ከሀገር አቀፉ ለውጥ በፊት ፖሊስ የህብረተሰቡን መብት ሊያስከብር ቀርቶ የራሱንም ድህነት ማረጋገጥ ተስኖት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ለውጡን ተከትሎ ችግሩ ከስር መሰረቱ በማስወገድ በአዳዲስ አደረጃጀቶች ፣ አሰራሮች ፣ ቴክኖሎጂዎችና ቅንጅታዊ በመፍጠር የመጡት ለውጦች በአስተዳደሩ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ እንዲሰፍን ማገዙን ተናግረዋል፡፡
እነዚህ ተግባራት ይበልጥ እንዲጠናከሩ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚረግ ገልፀው፤ የማዕረግ ሽግግሩ የበለጠ ህብረተሰቡን ዝቅ ብለው ፖሊስና አመራሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትጋት እንዲያገለግሉ የተሰጣቸው አደራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
የድሬዳዋ ፖሊስ አባላትና አመራሮች የምሥራቁን ቀጠናና የሀገርን ሰላም ከሌሎች የፍትህና የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በአስተማማኝ መንገድ የመጠበቅ ኃላፊነትን በላቀ ደረጃ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽነር አለሙ መግራ ናቸው ፡፡
በ16 ሚሊዮን የተገነቡት ፕሮጀክቶች ፖሊስ በእውቀትና በጉልበትና ከማስተባበር ውጪ በባለሃብቱና በህብረተሰቡ ድጋፍ የተገነቡ መሆናቸውን ገልፀው፤ ይህም ፖሊስና ነዋሪው ለሀገር ታላቅነት በጋራ መቆማቸውን ያረጋገጡበት ልማት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቆይታ ጊዜ ፣ የለውጥ ጉዞውን ስኬታማ በማድረግ ፣ በሀገር ህልውና ማስከበር ዘመቻ ግንባር ለዘመቱ፣ በሥነ ምግባር፣ በሥራ አፈጻጸምና በትምህርት ዝግጅት የማዕረግ ዕድገት ያገኙት አባላትና አመራሮች የተሰጣቸው ኃላፊነት የትኛውንም አካባቢያዊና ሀገራዊ ግዳጅ ለመወጣት ይበልጥ እንዳዘጋጃቸው ገልጸዋል፡፡
ከረዳት ሳጂንነት እስከ ኮማንደርነት ማዕረግ ለተሰጣቸው የፖሊስ አባላትና አመራሮች ማዕረግ ያለበሱት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባና የኢትዮጵያ የፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ናቸው፡፡
የዳቦ ቤት፣ የመዋኛና ሰው ሰራሽ ሣር የለበሰ መለስተኛ እግር ኳስ መጫወቻ ያካተቱት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሎች ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር፣ የምስራቅ ተጎራባች ክልሎች ኮሚሽነሮችና ከፍተኛ አመራሮች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ የኃይማኖት አባቶች ፣ ኡጋዞችና አበገዳዎች ተሣታፊ ሆነዋል፡፡
ነገ የምስራቅ ተጎራባች ክልሎች የሰላምና የፀጥታ ጉባኤ እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡