ቀጥታ፡

በወሊድ ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶች ሞት ለመቀነስ የግንዛቤ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት

አዲስ አበባ፣ የካቲት 05/2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ በወሊድ ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶች ሞት ለመቀነስ የግንዛቤ መፍጠር ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለፀ።

የዘንድሮው የጤናማ እናቶች ወር "በማንኛውም ሁኔታ ከወሊድ በኋላ በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶች ሞት እጅ ለእጅ ተያይዘን እንግታ'' በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ዳይሬክተር አቶ ፈቃዱ ማዘንጊያ፤ በኢትዮጵያ በወሊድ ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶች ሞት ለመቀነስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በወሊድ ሳቢያ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ከ2 ሺህ በላይ ሚድዋይፍች በእናቶች ጤና ላይ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በወሊድ ምክንያት ከሚሞቱ እናቶች መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት በሚያጋጥማቸው የደም መፍሰስ ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።

በመሆንም የእናቶችን ሞት በአንድ ሶስተኛ ለመቀነስ የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ሰፊ ንቅናቄ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ጤና አጠባበቅ ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም፤ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሚወልዱት 100 ሺህ እናቶች መካከል 401 የሚሆኑት በወሊድ ምክንያት ህይወታቸው እንደሚያልፍ ገልጸዋል።

የሞት ምጣኔው ካለፉት አምስት አመታት ጋር ሲነጻጸር 72 በመቶ መቀነስ ቢቻልም ከዚህ በላይ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በመሆኑም በ2030 ዓ.ም በወሊድ ምክንያት የእናቶችን ሞት ከ401 ወደ 70 ለመቀነስ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በየአመቱ በጥር ወር የሚከበረው የጤናማ እናቶች ወር በአለም ለ35ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም