የህብረት ስራ ኮሚሽን በቅናሽ ለገበያ ባቀረባቸው ምርቶች ተጠቃሚ ሆነናል - ኢዜአ አማርኛ
የህብረት ስራ ኮሚሽን በቅናሽ ለገበያ ባቀረባቸው ምርቶች ተጠቃሚ ሆነናል
አዲስ አበባ የካቲት 4/2014 (ኢዜአ) የህብረት ስራ ኮሚሽን በቅናሽ ለገበያ ባቀረባቸው ምርቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን ሸማቾች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ዘርፈ ብዙ አማራጮችን እያቀረበ ነው።
በተመረጡ ቦታዎች የእሁድ ገበያ በማዘጋጀት ሸማቹንና አምራቹን የማቀራረብ ስራ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።
በየዓመቱ በሚዘጋጀው የንግድ አውደ ርዕይ፤ ሁሉም ክልሎች ምርቶቻቸውን እንዲያቀርቡ በማድረግ ሸማቹንና አምራቹን በቀጥታ እንዲገናኝ ይደረጋል።
ከየካቲት 3 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በመዲናዋ በይፋ የተከፈተው ዘጠነኛው የህብረት ስራ የንግድ አውደ ርዕይ በቅናሽ ለገበያ ባቀረባቸው ምርቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው ሸማቾች ገልጸዋል።
ከአስተያየት ሰጭዎቹ መካከል አቶ ሙሉጌታ ተፈራ፤ በአውደ ርዕዩ የቀረቡት ምርቶች በዝቅተኛ ዋጋ የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ እና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።
የቀረቡት ምርቶች ትክክለኛ ቅናሽ የተደረገባቸው በመሆኑ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ያለው ደግሞ የተለያዩ ምርቶችን ሲሸምት ያገኝነው ወጣት ያሬድ ኪዳኔ ነው።
በመዲናዋ የተለያዩ ምርቶችን ዋጋ ለማረጋጋት አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑንም ተናግሯል።
ከምዕራብ ሀረርጌ ቡረቃ ጋለቲ ህብረት ስራ ማህበር ምርታቸውን ይዘው የቀረቡት ወይዘሮ አልማዝ ሃምዛ፤ ምርቶቹ ለገበያ የቀረቡት በቅናሽ ዋጋ መሆኑን ይገልፃሉ።
አውደ ርዕዩ ለአምራቹ የንግድ ትስስር ከመፍጠር በዘለለ የገበያውን ሁኔታ ለማረጋጋት መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ያሉት ደግሞ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ዳንጉር ወረዳ ምርታቸውን ያቀረቡት አቶ ሙሉአለም አያና ናቸው
እርሳቸው እንደሚሉትም ለገበያ የቀረቡት ምርቶች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉና ገበያን ማረጋጋት የሚችሉ ናቸው።
ኢግዚቪሽኑ ከየካቲት 3 እስከ የካቲት 7 ቀን 2014 ዓ.ም በኢግዚቤሽን ማዕከል እየተካሔደ ነው።