የትምባሆን የጤና ጠንቅነት እና ከሱሱ መላቀቅ የሚያስችሉ መንገዶችን ያካተተ መጽሀፍ ለንባብ በቃ - ኢዜአ አማርኛ
የትምባሆን የጤና ጠንቅነት እና ከሱሱ መላቀቅ የሚያስችሉ መንገዶችን ያካተተ መጽሀፍ ለንባብ በቃ
አዲስ አበባ የካቲት 4/2014 (ኢዜአ) የትምባሆን የጤና ጠንቅነት የሚያመላክት እና ከሱሱ ለመላቀቅ የሚያስችሉ መንገዶችን ያካተተ መጽሀፍ ለንባብ በቃ።
የመጽሐፉ ምርቃት ዛሬ የተካሄደ ሲሆን በርካታ የጥናት ውጤቶችን እና የፀሐፊውን የህይወት ተሞክሮ ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።
የመጽሀፉ ደራሲ አቶ ተካልኝ ለገሰ፤ ለ40 አመታት የትምባሆ አጫሽ ስለነበሩ ለልብ፣ ስኳር፣ የደም ግፊትና ሌሎች የጤና እክሎች ተዳርገዋል።
በመሆኑም ሌሎች ከእርሳቸው እንዲማሩ ለማድረግ የትምባሆን የጤና ጠንቅነትና ከሱሱ መላቀቅ የሚቻልባቸውን መንገዶች ለማመላከት መፅሃፍ መድረሳቸውን ገልጸዋል።
በአማርኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀው መጽሐፉ ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች ወስነው እንዲያቆሙ አጠቃላይ ማህበረሰቡም ትምህርት እንዲያገኝበት ታስቦ ተዘጋጅቷል።
"ትምባሆና የጤና ጉዳቶቹ" በሚል ርእስ የተዘጋጀው መጽሐፉ 116 ገጾችን ይዞ በ12 ምእራፎች የተከፋፈለ መሆኑን አቶ ተካልኝ ገልፀዋል።
በመፅሃፉ ምርቃት ላይ የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን የምርት ደህንነት ዳይሬክተር ወይዘሮ አስናቀች አለሙ መልእክት አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸውም የመፅሃፉ መዘጋጀት ትንባሆ የሚያስከትላቸውን የጤና ጉዳቶችና ከሱስ መውጣት የሚቻልባቸውን መንገዶች ለማመላከት ያግዛል ብለዋል።
የትምባሆ ምርቶች ላይ ታክስ እንዲጨመር ከማድረግ ጀምሮ ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ሲጋራ እንዳይጨስ የወጣው ሕግ ተግባራዊ እንዲሆን ባለስልጣኑ የቁጥጥር ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠሉንም ገልጸዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው በአለም ላይ በየአመቱ በትባሆ ወይም ሲጋራ በማጨስ ከ8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለህልፈት ይዳረጋሉ።
ከነዚህ መካከል በርካቶቹ በቀጥታ ትንባሆ በማጨስ የሚሞቱ ሲሆን 1 ነጥብ 2 ሚሊየኑ ግን ለጭሱ ተጋላጭ በመሆናቸው መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።