ቀጥታ፡

አንጋፋው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያስገነባው አዲስ ህንጻ ነገ ይመረቃል

አዲስ አበባ የካቲት 4/2014 (ኢዜአ) 80 ወርቃማ ዓመታትን ያስቆጠረው አንጋፋው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያስገነባው አዲስ ህንጻ በነገው እለት ይመረቃል።

በኢትዮጵያ 117 ዓመታትን ያልበለጠ እድሜ ባስቆጠረው የባንክ ስራ ታሪክ ትልቅ አሻራ ይዞ የዘለቀ የፋይናንስ ተቋም ነው፤የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ።

በ1935 ዓ.ም በ1 ሚሊዮን የማሪያትሬዛ መነሻ ካፒታል ‘የኢትዮጵያ መንግስት ባንክ’ በሚል የብሔራዊ ባንክን እና የንግድ ባንክን ሚና አጣምሮ በመያዝ ነበር የተመሰረተው።

በ1955 ዓ.ም ብሔራዊ ባንክ ሲቋቋም ‘የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ’ በሚል ስያሜ የአገሪቷን ገንዘብ ተቆጣጣሪነት ሚናውን በመተው በንግድ ሥራ ዘርፉን ይዞ ቀጠለ።

80 ዓመታትን ያስቆጠረው ይህ አንጋፋ ባንክ በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ ከ1 ሺህ 800 በላይ ቅርንጫፎች እና ከ34 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን አፍርቷል።

አሁን ላይ ጥቅል ተቀማጭ ገንዘቡን 824 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ጠቅላላ ሀብቱም 1 ነጥብ 1 ትሪሊዮን ብር አድርሷል።

ባንኩ በ2013 ዓ.ም ለተለያዩ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችና የንግድ ተቋማት 107 ቢሊዮን ብር በብድርና ቦንድ ሽያጭ ሲያቀርብ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ከብድር ተመላሸ ሰብስቧል።

በባንኩ የ80 አመታት ታሪክ ትልቅ የተባለውን የ20.3 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገብ መቻሉንም ባለፈው ዓመት አሳውቆ ነበር።

በተያዘው የ2014 ባጀት ዓመት ደግሞ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ለመስጠት ግብ ይዞ ወደስራ ገብቷል።

ከሚሰጣቸው ብድሮች መካከልም 25 ቢሊዮን ብር ለግሉ ዘርፍ፣ 30 ቢሊዮን ብር ለግብርና ግብዓት ሲሆን ቀሪው ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች እንደሆነ አሳውቋል።

ባንኩ በተደራሽነት፣ጥራት እና ቴክኖሎጂ መራሽ አገልግሎት ራሱን እያዘመነ ከምስረታው ጀምሮ በባንክ አገልግሎት ዘርፍ እና ማህበራዊ ኃላፊነቱ ሚናው ቀዳሚነቱን ይዞ 80 ወርቃማ ዓመታትን አሳልፏል፡፡

80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ሲያከብር ግን በአገሪቱ ብቻ ሳይሆን በቀጣናው ሰማይ ታካኪ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት ህንፃ ገንብቶ በነገው ዕለት ሊያስመርቅ ሽር ጉድ እያለ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም