በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችን ለማቅረብ አምራቾች በስልጠና ሊደገፉ እንደሚገባ ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችን ለማቅረብ አምራቾች በስልጠና ሊደገፉ እንደሚገባ ተመለከተ
ሀዋሳ፤ የካቲት 5/2014 (ኢዜአ) በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ የሆነ የቆዳ ውጤቶች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ለማቅረብ አምራቾች በስልጠና ሊደገፉ እንደሚገባ የዘርፍ ተዋናዮች ጠየቁ።
ለምርቶቹ ደረጃ ከማውጣት ባለፈ የቀንድ ከብት መረጣና የአትክልትና ፍራፍሬ ዘር አቅርቦት ላይ ያተኮረ ድጋፍ ላይ እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጄንሲ አስታውቋል።
የሶልጌት ሌዘር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ጌቱ ለኢዜአ እንደገለጹት በቆዳው ኢንዱስትሪ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት አለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶችን ማምረትና ተወዳዳሪ መሆን ያስፈልጋል።
የቀንድ ከብት ጤንነትን ከሚከታተለው በየደረጃው ከሚገኘው የግብርና ሴክተር ጀምሮ በኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ሙያተኞች ደረጃውን የጠበቀ ምርት ማምረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ግንዛቤ ሊኖራቸውና ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በዘርፉ ከ34 ዓመታት በላይ ልምድ እንዳላቸው የተናገሩት አቶ ሰለሞን፤ የኢትዮጵያ ቆዳ በአለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ መሆኑን ጠቁመው እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች በማምረት የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማስገኘት እንደሚገባ አመልክተዋል።
በሀገር ደረጃ የሚወጡ የምርት ጥራት ደረጃዎች ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርጉት አምራቹንና ላኪውን እንደሆነ ገልጸው ይሄም በስልጠና ሊደገፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የቆዳ ምርቶች እሴት ሰንሰለቱ ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት በመንግስት በኩል በፖሊሲ የተደገፈ ጣልቃ ገብነት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
አቶ ሰለሞን አክለው የኢትዮጵያን ምርት በአለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ የመንግስትና የግል ኢንዱስትሪዎች ተቀናጅተው መስራት እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።
በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ የተሰማሩት የጂ 2 ሆልቲካልቸር ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ አሰግደው በበኩላቸው ድርጅታቸው የሚያመርታቸውን ምርቶች ለአውሮፓ፣ ለመካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ ገበያዎች እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡
ጥራትን መሰረት ያደረገ ምርት በማምረት ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ከግለሰብ አምራች አርሶ አደሮች ጀምሮ ግንዛቤ መፍጠርና ላኪዎች ተቀናጅተው እንዲሰሩ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሲዳማ ክልል ዳሌ ወረዳ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች የሆኑት አርሶ አደር መንግስቱ አሊቶ ከስድስት ሄክታር በሚበልጥ ማሳ ላይ የተሻሻሉ የአቮካዶ፣የቡናና ሌሎችንም ልማቶች እያካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል።
በአቅራቢያቸው ለሚገኘው የይርጋለም የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክ የአቮካዶ፣ ምርታቸውን በማቅረብና የተሻሻሉ ዝርያዎችንም ለአርሶ አደሩ በመሸጥ ከአንድ ሄክታር የአቮካዶ፣ ማሳ እስከ 800 ሺህ ብር እንደሚያገኙ ገልጸዋል።
ከመልካሳ ግብርና ምርምር የሚያገኟቸው የተሻሻሉ የአቮካዶ ዝርያዎች ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርጓቸው ቢሆኑም ጥራት ያለው ምርት በማምረት ሂደት ከመንግስት ሙያዊ እገዛ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
በቆዳና ቆዳ ውጤቶችም ሆነ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ የሚታየው የጥራት ችግር ከዘር መረጣ የሚጀምርና ቅንጅታዊ ስራ የሚጠይቅ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጄንሲ የደረጃዎች ዝግጅት ዳይሬክተር አቶ ይልማ መንግስቱ ናቸው።
ችግሩን በመሰረታዊነት ለመፍታት ደረጃ ከማውጣት ባለፈ የላኪና አምራች አርሶ አደሮችን ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚያስችል ተከታታይ ስልጠና ለመስጠት አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ባለድርሻ አካላት እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች በማምረት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ማሳደግ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።
ኤጄንሲው በቆዳና ቆዳ ውጤቶች እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ለተሰማሩ ባለድርሻ አካላት በሀዋሳ ከተማ ለሁለት ቀናት ያዘጋጀው የምክክር መድረክ በትናንትናው እለት መጠናቀቁ ይታወቃል።