በፌደራል ደረጃ ያለው የንግድ ፈቃድ አሰጣጥና ምዝገባ በውክልና ወደ ክልሎች ሊወርድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በፌደራል ደረጃ ያለው የንግድ ፈቃድ አሰጣጥና ምዝገባ በውክልና ወደ ክልሎች ሊወርድ ነው
ባህር ዳር ነሐሴ 25/2010 በፌደራል ደረጃ ብቻ ሲሰጥ የቆየው የአስመጪዎችና ላኪዎች የንግድ ፈቃድ አሰጣጥና ምዝገባ ስርዓትን በውክልና ወደ ክልሎች ለማውረድ እየተሰራ መሆኑን የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ። ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል ለሚገኙ አስመጪዎች በባህርዳር ከተማ የግንዛቤ ማጎልበቻ ስልጠና እየተሰጠ ነው። በሚኒስቴሩ የገቢ ንግድ ስራ አመራር ክትትልና ድጋፍ ቡድን መሪ አቶ ሳሙኤል ግዛው እንደገለጹት የአስመጪና ላኪ ንግድ እንቅስቃሴውን ቀላልና ቀልጣፋ ለማድረግ የአሰራር ማሻሻያ እየተደረገ ነው። ለዚህም ለረጅም ጊዜ በፌደራል ደረጃ ሲሰጥ የቆየውን የአስመጪዎችና ላኪዎች የንግድ ፈቃድ አሰራር ወደ ክልሎች በማውረድ ነጋዴዎቹ በቅርበት አገልግሎቱን እንዲያገኙ እየተመቻቸ መሆኑን ተናግረዋል። ማሻሻያውም በአዲስ አበባ መርካቶ ብቻ ተይዞ የቆየውን የአስመጪነትና የላኪነት ንግድ ስራ ተደራሽ በማድረግ ክልሎች የሚያስፈልጓቸውን ዕቃዎችና ሸቀጦችን የራሳቸው ባለሃብቶች ፈጥነው እንዲያስመጡ ያስችላል። የንግድ ፈቃድ አሰጣጥና ምዝገባ ስርዓቱን ወደክልሎች ማውረድ ያስፈለገውም ጥራት ያለው ምርት በአነስተኛ ወጪ በቀጥታና በፍጥነት በማስመጣት በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ተደራሽ እንዲሆን ዓላማ ያደረገ ነው። የየክልሉ ንግድ ቢሮዎች የውክልና ኃላፊነት ወስደው የአስመጪነትና ላኪነት ፈቃዱን በተያዘው በጀት ዓመት እንዲሰጡ ለማድረግ የማሳወቅና የዝግጅት ስራ ተጀምሯል። ክልሎቹ ላኪዎችንና አስመጪዎችን ፈቃድ ከመስጠት ባለፈ የክትትልና የድጋፍ አገልግሎት እንደሚሰጡ የጠቆሙት ቡድን መሪው ከንግድ ሚኒስቴር ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት በሪፖርት ላይ የተመሰረተ እንደሚሆንም ጠቁመዋል። "ሚኔስቴሩ ከክልሉ ንግድ ቢሮ ጋር በመተባበር በክልሉ ለሚገኙ 100 አስመጪዎች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ስልጠና መስጠት መጀመሩ በገቢ ንግድ ዙሪያ ያሉ ማነቆዎችን በቀላሉ መፍታት ያስችላል "ብለዋል። የአማራ ክልል ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው የንግድ ስርዓቱን ለማዘመን የአስመጪዎችና ላኪዎችን አቅም ማጎልበት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ " ተወዳዳሪነትና ጥራት ያለው ምርት ወደክልሉ ውስጥ በማስገባት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ አቅርበው በመሸጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ያስቻላል" ብዋል። የገቢና ወጭን ንግድ ሚዛኑን ለማስተካከል ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት መንግስት ለማምረቻው ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። በተለይ በፌደራል ደረጃ ሲሰጥ የቆየው የፈቃድ አሰጣጥ ስርዓት ወደክልሎች እንዲወርድ እየተሰራ ያለውም አስመጪዎችና ላኪዎች የሚያጋጥማቸውን ውጣ ውረዶች የሚያስቀር ነው። ይህም አስመጪዎችን እየተፈታተናቸው የሚገኙትን የንግድ ፈቃድ አወጣጥ፣ የወደብ፣ የካፒታልና መሰል ችግሮችን በቀላሉ መፍታት ያስችላል፡፡ በክልሉ ከ400 በላይ አስመጪ ነጋዴዎች እንደሚገኙ የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ እንግዳወርቅ ኪዳኔ ናቸው። "ለነዚህ ነጋዴዎች ተከታታይ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎችን መስጠት ተወዳዳሪ ሆነው በመውጣት ከራሳቸው አልፈው ሀገራቸውንና ክልላቸውን እንዲጠቅሙ ያስችላል" ብለዋል። የአስመጪዎችና ላኪዎች ፈቃድ አሰጣጥና እድሳት በክልሎች የሚያልቅበትን አሰራር ለመዘርጋት እየተደረገ ያለው ጥረትም የንግድ አሰራሩን ለማቀላጠፍ ያግዛል። በዳንግላ ከተማ ነዋሪ የሆኑትና በጣውላ አስመጪነት ንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ አስማረ አቤ ፈቃዱን በ2009 ዓ.ም ቢያወጡም በውጭ ምንዛሬ ዕጥረት እስካሁን ወደስራ እንዳልገቡ ተናግረዋል፡፡ " አሰራሩ ወደክልሉ የሚወርድ ከሆነና በአቅራቢያችን የሚገኙ የአሰብና የምፅዋ ወደቦችን የምንጠቀም ከሆነ እየተሰጠ ባለው ስልጠና አቅሜን አጎልብቼ የተሻለ ስራ እንድሰራ ያግዘኛል" ብለዋል። ሰልጣኞቹ በቆይታቸው በባንክ ንግድ አሰራር፣ በገቢዎችና ጉምሩክ፣ በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ እንዲሁም በባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አሰራር ላይ አተኩሮ ትምህርት እየተሰጠ ነው።