የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን መድሀኒቶች በሲሚንቶ ጭነት ስር ደብቆ ወደ መሀል ሀገር ሊያስገባ የነበረ አሽከርካሪ ተያዘ - ኢዜአ አማርኛ
የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን መድሀኒቶች በሲሚንቶ ጭነት ስር ደብቆ ወደ መሀል ሀገር ሊያስገባ የነበረ አሽከርካሪ ተያዘ
ጭሮ፤የካቲት 5/2014(ኢዜአ) የማረጋገጫ ፈቃድ የሌላቸውና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን መድሀኒቶች በሲሚንቶ ጭነት ስር ደብቆ ወደ መሀል ሀገር ለማስገባት የሞከረ አሽከርካሪ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።
የጭሮ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ዋና ሳጅን ካሳሁን ባይሳ ለኢዜአ እንደገለጹት አሽከርካሪው በቁጥጥር ስር የዋለው ትላንት ከምሽቱ 5፡00 ላይ ነው።
አሽከርካሪው የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3- 80691 አ.አ በሆነ ኤፍ ኤስ አር ተሽከርካሪ በሲሚንቶ ጭነት ስር መድሀኒቱን በመደበቅ ከሀረር ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ እንዳለ በጭሮ ኬላ በተካሄደ ፍተሻ በቁጥጥር ስር ውሏል።
ለራስ ምታትና ጀርባ ህመም እንዲወሰዱ የተዘጋጁ፣ የማረጋገጫ ፈቃድ የሌላቸውና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድሀኒቶች በፍተሻው መያዛቸውን ተናግረዋል ።
የተያዙት አምስት ቦንዳ መድሀኒቶች ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው መሆኑን አመልክተዋል።
አሽከርካሪው በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑን ዋና ሳጅን ካሳሁን አስታውቀዋል።