ቀጥታ፡

"ግብፅና ሱዳን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ መደገፍ አለባቸው"- አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

የካቲት 5 ቀን 2014 (ኢዜአ)የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በፍጥነት እንድታጠናቅቅ ግብፅ ማበረታታት አለባት ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናገሩ።

ሚኒስትር ዴኤታው ከአል-አረቢያ ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቆይታ የግድቡ መገንባት ግብፅን በድርቅ ወቅት እንኳ የውሃ ቋት ሆኖ የሚያገለግል ፕሮጀክት በመሆኑፕሮጀክቱን ልትደግፈው እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሱዳን በአነስተኛ ግድቦቿ ላይ ይደርስብኛል ብላ የምታነሳውን የደህንነት ስጋት በሚመለከት መደበኛ የሆነ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ ኢትዮጵያ ዝግጁ እንደሆነች አቋሟን አስርድታለች ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ሀገሪቱ ግን አሁን ላይ የራሷን ብሄራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ ይልቅ የሶስተኛ ወገን ጉዳይ አስፈፃሚ አየሆነች መምጣቷን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ አንድ ወገን ብቻ ከአባይ ሀብት ተጠቃሚ ሲሆን ዘላለም አለሟን መጠበቅ አትችልም ያሉት አምባሳደር ሬድዋን: በመሆኑም ሱዳን እና ግብፅ አሁን ከያዙት ግትር አቋም መላቀቅ አለባቸው ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ተቀመጫነቱን ዱባይ ካደረገው የአል-አረቢያ ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ በሚመለከት ብዙ አዎንታዊ የሆኑ እድሎችን አቅርባ እንደነበር የገለፁ ሲሆን ግብፅና ሱዳን ባለመቀበላቸው ምክንያት ሳይሳኩ እንደቀሩ ጠቁመዋል።

የህዳሴ ግድብ ከጭቅጭቅ ይልቅ የቀጠናዊ ህብረትና አንድነት ማሳያ ነው ያሉት አምባሰደር ሬድዋን ኢትዮጵያ በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ላይ ምንም አይነት የጎላ ጉዳት ሳታደረስ የራሷን ሀብት መጠቀም ትችላለች ብለዋል።

የሱዳንን አሁናዊ የፖለቲካ ሁኔታ በሚመለከት ሁሉም ወገኖች ከምንም በላይ ሀገራቸውን ማስቀደምና የሱዳናዊያንን ጥቅም ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

ሁሉም ፓርቲዎች የሀገሪቱን ዜጎች ጥቅም ከሁሉ ነገር በላይ በማስቀደም ነገሮችን በእርጋታና ምክንያታዊነት የሚያስኬዱ ከሆነ ልዩነቶቻቸውን ማስታረቅ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

በሱዳን ያለውን ቀውስ ለመፍታት በኢትዮጵያ በኩል የታየ ተነሳሽነት ካለ በሚል ከጋዜጠኛዋ ለቀረበላቸው ጥያቄ አምባሳደር ሬድዋን የሱዳን ህዝብ ችግሮቹን ያለማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት የመፍታት ጥበብ እንዳለው አስረድተዋል።

ለኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይን ለመቋጨት ወታደራዊ ሀይል በምንም መልኩ ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም ያሉ ሲሆን አስፈላጊው ነገር ኢትዮጵያ እንዳደረገችው የተሻለ የመፍትሄ ሀሳብ ወደ ጠረጴዛ ይዞ መቅረብ ነው ብለዋል።

ወደ ትግራይ ክልል የሚቀርብ የእርዳታ ድጋፍን በሚመለከትም ምንም እንኳን ታጣቂ ቡድኑ የሰብዓዊ ድጋፍ በተገቢ መልኩ እንዳይቀርብ እንቅፋት እየሆነ ቢሆንም የኢትዮጵያ መንግስት ግን ከሰብዓዊ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ያልተገደበ ድጋፍ በክልሉ እንዲደረግ የሚችለውን ሁሉ እያከናወነ መሆኑን ኤፍ ቢሲ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ ባለው ግጭት የውጭ ጣልቃ ገብነትን በሚመለከትም በርካቶች ኢትዮጵያን የማዳከም ፍላጎት እንዳላቸው መንግስት ጠንቅቆ ያውቃል ብለዋል።

አብዛኞቹ ጣልቃ ገብነቶችም መንግስት ያከናወናቸውን መልካም ስራዎች ላለማበረታታትና ዝቅ ለማድረግ መሆኑን አምባሳደር ሬድዋን ከአል- አራቢያ ጣቢያ የአረቢኛ ክፍል ባልደረባ ጋር በነበራቸው ቆይታ ላይ ተናግረዋል ሲል የቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም