ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በስፋት ለማካሄድ ትኩረት ተሰጥቷል

ሀዋሳ፤ የካቲት 4/2014 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል ያለውን የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ኃይል በማስተባበር የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በስፋት ለማካሄድ ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ።
 ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ   የተመራ የክልሉ የስራ ሃላፊዎችና የግብርና ባለሙያዎች በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተከናወነ ያለውን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ዛሬ በመስክ ተመልክተዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በዚህ ወቅት ለኢዜአ እንዳሉት፤ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለስንዴ ግዢ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስቀር ነው።

የልማት ስራው  እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን አመልክተው፤ እምቅ የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ኃይል እያለ ዘርፉ ለዘመናት ጥቅም ላይ ያልዋለ መሆኑን ተናግረዋል።

''ይህንን ሥራ ስንጀምር ያለ በቂ ልምድና የቴክኖሎጂ ግብዓት ነው'' ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ አርሶ አደሩ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች፣ ባለሙያዎችና አመራሩ  የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በዘርፉ ተግተን ከሰራን በሀገር ኢኮኖሚና በምግብ ዋስትና ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት ይቻላል ነው ያሉት ።

በቀጣይ በሲዳማ ክልል ያለውን የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ኃይል በማስተባበር  ልማቱን በስፋት ወደ ስራ ለማስገባት ዝግጅት እንደሚደረግ የጠቆሙት አቶ ደስታ፤ የከርሰ ምድር ውሃ አቅምን ለማጎልበት ከማጥናት ባለፈ የውሃ ጉድጓዶችን የማስቆፈር ስራ ይሰራል ብለዋል።

የገፀ ምድር ውሃ አቅሞችን ጥቅም ላይ ማዋል እንዲቻል አነስተኛ የመስኖ ግድቦችን የማስፋፋት ሥራ እንዲሁ።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ክፍሌ ሻሾ በበኩላቸው፤ዘንድሮ በክልሉ የበጋ መስኖ ስንዴ በሙከራ ደረጃ በ160 ሄክታር ላይ ለማልማት መታቀዱን ተናግረዋል።

እስካሁንም  138 ሄክታር ማሳ በአርሶ አደሮችና በግል ባለሀብቶች ማልማት መቻሉን አስታውቀዋል።

በቆሎ የሚመረትባቸው ቆላማ አካባቢዎች ላይ በበጋ ስንዴን በስፋት ማምረት እንደሚቻል ለአርሶ አደሮች በቂ ማሳያ መገኘቱንም አስረድተዋል።

አጠቃላይ በስንዴ ከተሸፈነው ማሳ በአማካይ በሄክታር 40 ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

ዘንድሮ ከ300 በላይ አርሶ አደሮች የበጋ መስኖ ስንዴን በሙከራ ደረጃ ማልማታቸውን ጠቅሰው፤ ይህንን ሥራ ለማስፋት የቅድመ ዝግጅትና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ይሰራል ብለዋል።

 ''ያየነው ውጤት ተስፋ ሰጥቶናል'' ያሉት ደግሞ በሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ 108 ሄክታር ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ እያለሙ ያሉት ደግሞ በዘርፉ የተሰማሩት ባለሀብት አቶ በላይ ባዴ ናቸው።

ከ450 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውን የገለጹት አቶ በላይ ፤አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይ ጊዜያት ከ500 ሄክታር በላይ የማልማት ዕቅድ እንዳላቸውም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም