ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲቲንግ ዘርፍን የሚደግፍ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4/2014 (ኢዜአ)  በኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲቲንግ ዘርፍን የሚደግፍ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።

ዓለም አቀፉ የአካውንቲንግ ቀን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ የተከበረ ሲሆን፤ በመርሃ-ግብሩም የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ እና የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ማህበር ፕሮጀክቱን ይፋ አድርገዋል።

በፕሮጀክቱ አማካኝነት የሂሳብ አያያዝ ሙያን ለመደገፍ እና በዘርፉ ያሉ የባለድርሻ አካላትን ፍላጎቶች ለማሟላት የሚያስችል ጠንካራ ስትራቴጂ ያለው ብሔራዊ  ተቋም እንደሚቋቋምም ተጠቁሟል፡፡

ፕሮጀክቱ በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት እንደሚከናወንም ነው የተገለጸው፡፡

የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር ሂክመት አብደላ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ፕሮጀክቱ በዘርፉ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የሚያሟላ የቁጥጥር ስርዓት ለመዘርጋት እንደሚያስችል አብራርተዋል፡፡

ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ ተፈላጊ የሆኑ ብቃት ያላቸው የሂሳብ ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደሚያግዝም ነው ያነሱት፡፡

የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ማህበር ስራአስኪያጅ ወይዘሮ ዮዲት ካሳ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያስችል ተቋማዊ አሰራር እንደሚፈጥር አውስተዋል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ የፋይናንስ ሪፖርቶች ለህዝብ ይፋ ከመሆናቸው በፊት ትክክለኝነታቸውን እንዲያረጋግጥ የሚያስችለውን አቅም እንዲያጎለብት ያግዛል ነው ያሉት፡፡

ይህንንም ለማሳካት ቀደም ብሎ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መሰጠታቸውን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም