ቀጥታ፡

የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ ምርቶችን በስፋት ማምረት ይገባል

አዲስ አበባ የካቲት 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ ምርቶችን በስፋት ማምረት እንደሚገባ የግብርና እና የምግብ ሳይንስ ምሁራን ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የአመጋገብ ባህል ሊሻሻል እንደሚገባም ነው የጠቆሙት፡፡
በአፍሪካ፣ በግጭት፣ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተጽዕኖ፣ በድርቅና አንበጣ መንጋ ምክንያት ከ280 ሚሊዬን በላይ ዜጎች ለረሃብና ምግብ እጥረት ተዳርገዋል፡፡

በተመሳሳይ በኢትዮጵያም በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች፣ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና በሌሎች ምክንያቶች በርካታ ዜጎች ለምግብ እጥረት ተዳርገዋል፡፡

የግብርና ልማት ተመራማሪ የሆኑት አቶ አብርሃም ቱራ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትና የምግብ ተደራሽነት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዋነኞቹ ምሶሶዎች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የአገር ውስጥ የምግብ ምርት ዝርያዎችን በቴክኖሎጂ በማበልጸግ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት፡፡

መንግስት ኢትዮጵያ ያላትን ዓመቱን ሙሉ መልማት የሚችል የእርሻ መሬት፣ በቂ ውሃ፣ እንዲሁም ተስማሚ የአየር ንብረት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡

በተለይም መንግስት በስፋት ከሚመረቱ እንደ ቡና፣ ሰሊጥና መሰል የወጪ ገበያ ተኮር ምርቶች በተጓዳኝ ለምግብ ፍጆቻ በሚውሉ እንደ ስንዴ፣ ሩዝ፣ ዘይት የመሳሰሉ ምርቶች ላይ ማተኮር አለበት ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተጀመሩት ሰፋፊ እርሻ ስራዎች አብዛኞቹ በመንግስት ስር መሆናቸውን ያስታወሱት አቶ አብርሃም፤ ከዚህ አኳያ በምግብ ፍጆታ ምርቶች ላይ የሚሳተፉ ባለሃብቶችን ማበረታታት ይገባል ነው ያሉት፡፡

መንግስት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያከናወኑ ስራዎችን የሚመራበት ግልጽ ፖሊሲና ስትራቴጂ መንደፍ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምግብ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ይሄኔ አየለ በበኩላቸው በምድር ላይ ለምግብነት የሚያገለግሉ ከሰባት ሺህ በላይ የዕፅዋት ዝርያዎች ቢኖሩም፤ 95 በመቶ የሚሆነው የዓለም ህዝብ በዋናነት ሩዝ፣ ስንዴና በቆሎ ብቻ እንደሚጠቀም አብራርተዋል፡፡

ይህ ምግብን ያለማመጣጠን ባህል ደግሞ ለምግብ ዋስተና መረጋገጥ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩን አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያም ምግብን አመጣጥኖ የመመገብ  ችግር መኖሩን አንስተው፤ በኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች ችግሩ  በስፋት እንደሚስተዋል ተናግረዋል፡፡

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አንድ ሰው በቀን ዘጠኝ የምግብ አይነቶችን አሰባጥሮ መመገብ ሲገባው በኢትዮጵያ ያለው የአመጋገብ ስርዓት ከሶስት የምግብ አይነቶች እንደማይዘል ለአብነት አንስተዋል፡፡

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሌላኛው ሁነኛ መፍትሄ በየአካባቢው የሚገኙና ለምግብነት የሚውሉ ምርቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባም ገልጸዋል ዶክተር ይሁኔ፡፡

በደቡባዊ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በብዛት ጥቅም ላይ የሚውለውና ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ያለው የእንሰት ምርት በሰሜኑ ክፍል ጥቅም ላይ አለመዋሉ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ችግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በቀላሉ የሚበቅለው፣ ከፍተኛ ፕሮቲን ያለውና በአውሮፓ ለመድሃኒትነት እየተሸጠ የሚገኘው ሳማ በኢትዮጵያ ከዚህ ግባ የሚባል ጥቅም ላይ አልዋለም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም