ቀጥታ፡

ሚኒስቴሩ የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ተማሪዎች የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ ነሀሴ 25/2010 የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ተማሪዎች ግምቱ 80 ሺህ ብር የሚያወጣ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ድጋፍ አደረገ። ሚኒስቴሩ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ለ100 የሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የትምህርት መርጃ መሳሪያ ድጋፍ አድርጓል። ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ለተወጣጡት እነዚህ ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው ቦርሳ፣ አንድ ደርዘን ደብተርና 10 እስክሪብቶ ተሰጥቷቸዋል። የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ የተጀመረውን የመረዳዳትና የአንድነት እሳቤን ለማጎልበት ሁሉም ተቋማትና የህብረተሰቡ ክፍሎች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አገራዊ ለውጡን በሚደግፉ ሌሎች መሰል ተግባራት ላይም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። ''የ'ፍቅርና የመደመር አገራዊ ጉዞ' እንዲሳካ በሁሉም ተግባራት እርስ በእርሳችን ልንረዳዳ ይገባል'' ብለዋል። የኢትዮዽያ ቀይ መስቀል ማህበር የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ  ጽህፈት ቤትን በመወከል የተገኙት አቶ ሽመልስ ማሬ በበኩላቸው በቀጣይ ተመሳሳይ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን ከፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እንደሚሰሩ ገልጸዋል። የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዳነ ሱሌ ለተማሪዎቹ የተደረገው የትምህርት መርጃ መሳሪያ ድጋፍ የነገ አገር ተረካቢ ተማሪዎች ላይ የመረዳዳትና የአንድነት ባህል በተግባር እንዲማሩ የሚያሳይ እንደሆነ አስረድተዋል። እንዲህ ዓይነቱ ድጋፍ ህብረተሰቡ ከገንዘብ ድጋፍ ባሻገርም ሁለገብ በሆነ እንቅስቃሴዎች ላይ የእርስ በርስ መተሳሰብና መረዳዳት ባህሉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም