ቀጥታ፡

"በአፍሪካ የአገርን ጥቅም ለማስጠበቅ ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራ መሪ በአንዳንድ የምእራቡ ዓለም አገራት ተቀባይነት ያጣል"

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4/2014 (ኢዜአ)  በአፍሪካ የአገርና ህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራ መሪ በአንዳንድ የምእራቡ ዓለም አገራት እምብዛም ተቀባይነት የማይኖረው መሆኑን አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ተናገሩ።

አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ለሰላሳ ዓመት በዘለቀ የስራ ዘመናቸው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአማካሪነት እስከ አምባሳደርነት አገልግለዋል፡፡

በቤልጂየም ብራሰልስ በአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ አምባሳደር እንዲሁም በኒውዮርክ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለ15 ዓመታት የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን አገልግለዋል።

በቀድሞዋ ዴሞክራቲክ ጀርመን፣ በደቡብ ኮሪያ እና በጋና ለዘጠኝ ዓመታት አምባሳደር በመሆን አገራቸውንና ህዝባቸውን አገልግለዋል፡፡

በዲፕሎማትነት አገራቸውን ለረጅም ዓመታት በማገልገል የካበተ ልምድ ያላቸውን አምባሳደር ጥሩነህ ዜና፤ የኢትዮጵያን አሁናዊ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ በተመለከተ ኢዜአ አነጋግሯቸዋል።

ኢትዮጵያ ችግር በገጠማት ወቅት ፊታቸውን የሚያዞሩ አገራት ጥንትም ነበሩ፣ አሁንም አሉ፣ ወደፊትም ይኖራሉ የሚሉት አምባሳደር ጥሩነህ፤ የዲፕሎማሲ ስራ የማይቋረጥና ቀጣይነት የሚኖረው ነው ሲሉ አስረድተዋል።

የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ ቢሞከርም በዲፕሎማሲ ጥረትና እውነታን በማስረዳት በኢትዮጵያ ላይ እምነት አድሮ ጉባኤው በስኬት መከናወኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው አትራፊ መስክ አትራፊ የሆነችበት፣ መልካም ገፅታዋን የገነባችበት እንዲሁም በኢትዮጵያ በኩል የሚነሱ ሀሳቦች ጎልተው የወጡበት መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ላይ ፊታቸውን ያዞሩ አንዳንድ አገራት የህዝቡን ውስጣዊ መሰረትና ለአገር ህልውና ማስጠበቅ ህዝቡ ያለውን ቁርጠኝነት በውል ባለመገንዘባቸው መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ህልውና ጉዳይ የማይደራደሩና ዘላለማዊ ክብሯን ለማስጠበቅ የቆሙ በመሆናቸው "ፅኑ መሰረቷ ሊናጋ ነው" ብለው በማሰብ ፊታቸውን አዙረው የነበሩ አገሮች ተጨባጩን እውነታ እየተረዱት ይመጣሉ ብለዋል።

ከዲፕሎማሲ ልምዳቸው በመነሳት "ምዕራባውያን ሲያሞካሹን እንጂ ሲቃወሙን አልደነግጥም" ያሉት አምባሳደር ጥሩነህ፤ በተለይም በአፍሪካ የአገርና ህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራ መሪ በምእራቡ ዓለም አገራት እምብዛም ተቀባይነት አይኖረውም ሲሉ አስረድተዋል።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ "ኢትዮጵያ እኔ ያልኩትን ካልፈፀመች" በሚል በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በግልጽ ያሳዩት አቋም ጥሩ ማሳያ መሆኑንም አንስተዋል።

በዲፕሎማሲው መስክ እንደነዚህ አይነት አቋሞች የሚያራምዱት እውነታው ጠፍቷቸው ሳይሆን ከራስ ጥቅምና ፖለቲካዊ ፍላጎታቸው የሚመነጭ መሆኑን ገልጸዋል።

በአድዋ ጦርነት የኢትዮጵያን ድል አድራጊነት የመላ ጥቁር ህዝቦች ድል ማድረግ እንደተቻለ ሁሉ በአፍሪካ መድረክ የመሪነት ሚናዋን አስጠብቆ ለመቀጠል ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላምና ነፃነት፣ ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ እና ሌሎችም አህጉራዊ ጉዳዮች ያላትን የጎላ አስተዋፅኦ አሁንም ማስቀጠል አለብን ብለዋል፡፡

የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ገፅታዋ ይበልጥ እየተሻሻለ ፓርኮች፣ መዝናኛዎች፣ የስልጠና ማዕከላትና ተቋማት አፍሪካዊነትን በቅጡ እንዲላበሱ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የፓን አፍሪካኒዝምን ታሪክ ከሚያጠኑ ተቋማት ጋርም በትብብር መስራትና ሃሳብ መለዋወጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም