ቀጥታ፡

በምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍል በኩል ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች ከ215 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

ድሬዳዋ፤ የካቲት 4/2014 (ኢዜአ) በምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍል በኩል ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች ከ215 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የድሬዳዋ ውጭ ንግድ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ሐድጎ  ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ገቢው የተገኘው ከቡና፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ጫት፣ ጥራጥሬ፣ ቁም እንስሳትና ከሌሎች የግብርና ምርቶች  ነው፡፡

ምርቶቹ  የተላኩት ወደ ምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ፣ ጀርመን፣ ጃፓንና አሜሪካ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ገቢው በግማሽ የበጀት ዓመቱ  ለማግኘት ከታቀደው 95 ነጥብ 5 በመቶ ቢሆንም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር  ሲነጻጸር የ3 ነጥብ 8 በመቶ  ብልጫ አለው ብለዋል፡፡

እቅዱን ማሳካት ያልተቻለው ከጥቅምት ወር ጀምሮ የነበረው ደረቃማ የአየር ንብረት በግብርና ምርቶች ላይ ተፅዕኖ በማሳደሩ ነው አቶ ተስፋዬ  ተናግረዋል፡፡

በቁም እንስሳት ላይ የሚስተዋለው የኮትሮባንድ ንግድ  አለመቆሙ ከዘርፉ ይገኝ የነበረው  የውጭ ምንዛሬ  ገቢ  እንዲቀንስ ማድረጉንም አስረድተዋል፡፡

በቀጣይ በኮትሮባንድ ንግድ ላይ የጠበቀ ቁጥጥር በማድረግና የ"ኳራንቲን" ጣቢያዎችን በሰው ኃይልና  በቁሳቁስ በማጠናከር ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ የማሳደግ የተቀናጀ ሥራን ይጠይቃል  ብለዋል፡፡

ከድሬዳዋ የንግድ ማህበራት መካከል የቢፍቱ አዱኛ አክሲዮን ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ያሲን መሐመድ፤ በግማሽ የበጀት ዓመቱ ወደ ውጭ ከላኩት የጫት ምርት የ5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

ማህበሩ 10 ሺህ አርሶ አደሮች የአትክልትና ፍራፍሬ በጥራት እንዲያመርቱና በሚመረተው ምርት ላይ እሴት በመጨመር ወደ ውጭ በመላክ የተሻለ የውጪ ምንዛሬ ለማግኘት እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም