ቀጥታ፡

የህፃናት አድን ድርጅት በአሸባሪው ለተጎዱ ወገኖችና ተቋማት 23 ሚሊየን ብር የሚገመቱ ቁሳቁሶች አበረከተ

ሰቆጣ ፤ የካቲት 4/2014 (ኢዜአ) የህፃናት አድን ድርጅት በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሄረሰብ ዞን አሸባሪው የህወሃት ቡድን ፈጽሞት በነበረው ወረራ ለተጎዱ ወገኖችና ተቋማት ድጋፍ የሚውል 23 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው ቁሳቁሶችን አበረከተ።

በርክክቡ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ  በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን እንዳሉት፤ የሽብር ቡድኑ በክልሉ ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች በርካታ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት አድርሷል።


በዚህም በሽብር ቡድኑ ዘረፋና ውድመት የደረሰባቸውን ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ለማስገባት የግብረ ሰናይ ድርጅቶችና የባለሃብቶች ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የህፃናት አድን ድርጅት በዞኑ ያደረገው ድጋፍ በሽብር ቡድኑ  የወደሙ የጤና ተቋማትን ወደ ሙሉ አገልግሎት መስጠት እንዲመለሱ የሚደረገው ጥረት የሚያግዝ ነው ብለዋል።

ድርጅቱ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት አቶ ስዩም፤ ሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶችም የሰብአዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋም ላይ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ  ጠይቀዋል።

በህፃናት አድን ድርጅቱ የኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር አቶ አሸብር ደበበ በበኩላቸው፤ የህፃናት አድን ድርጅት በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ በህፃናት ደህንነትና ስርዓተ ምግብ መሻሻል ላይ ሲሰራ መቆየቱን አውስተዋል።

ድርጅቱ አሁን ደግሞ በነበረው የጸጥታ ችግር  ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎችና ተቋማት 23 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው ቁሳቁሶች አበርክቷል።

ለ3 ሆስፒታሎች ፣ለ20 ጤና ጣቢያዎች የሚያገለግሉ መድሃኒቶች፣ የህሙማን መኝታ ፍራሾች፤ የተማሪዎች መማሪያ ደብተርና እስክብሪቶ ፣  ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ፍራሽና ብርድ ልብስ  ድርጅቱ ካበረከታቸው ቁሳቁሶች ይገኙበታል።

በቀጣይም ድርጅቱ የሚያደርገውን የሰብአዊ ድጋፎችና የፕሮጀክት ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

በሽብር ቡድኑ ወረራ ምክንያት በርካታ ዜጎች በጤናና ምግብ አቅርቦት እጥረት  መጎዳታቸውን  የገለጹት ደግሞ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ ገብሬ ናቸው።

የህፃናት አድን ድርጅቱ ያደረገው ድጋፍ ለዜጎች የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻልና ከትምህርት ገበታ ውጭ የነበሩ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ለመመለስ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተናገረዋል።

ከድጋፍ ርክክቡ በኋላ  የክልል፣ የዞንና የህፃናት አድን ድርጅት አስተባባሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሽብር ቡድኑ ጉዳት የደረሰባቸውን የተፈራ ሃይሉ መታሰቢያ ጠቅላላ ሆስፒታል፣ የሰቆጣ ጤና ጣቢያንና የአዝባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም