በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞች የመብት ጥሰት እየተፈፀመባቸው መሆኑ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞች የመብት ጥሰት እየተፈፀመባቸው መሆኑ ተጠቆመ
አዲስ አበባ ነሀሴ 25/2010 በቱሪስት ቪዛ ሽፋን በህገወጥ ደላሎች ከአገር ወጥተው በሊባኖስ የሚገኙ የቤት ሰራተኞች የመብት ጥሰት እየተፈፀመባቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን አስታወቀ። በኤርትራ ካለው አቻ የሰራተኞች ኮንፌዴሬሽን ጋር ግንኙነት ለመፍጠር በነገው ዕለት የኮንፌዴሬሽኑ የልኡካን ቡድን ወደ ኤርትራ እንደሚያቀና ተነግሯል። የተሻለ ስራ ፍለጋ የሚደረግ ህጋዊ ሽፋን ያለው ህገወጥ የዜጎች ዝውውርን አስመልክቶ ኮንፌዴሬሽኑ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከተው፤ በሐምሌ ወር ላይ በሊባኖስ በተደረገ የስራ ጉብኝት በአገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞች ያሉበትን ሁኔታ መመልከት ተችሏል። በዚህም ኮንፈዴሬሽኑ ባደረገው ጉብኝት በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞች ላይ ድብደባና የአካል መጉደልን ጨምሮ አስከፊ የመብት ጥሰቶች እንደሚፈፀምባቸው እስከሞት የሚደርስ ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሆነ ማረጋገጡን ይፋ አድርገዋል። በተለይ በህገወጥ ደላሎች አማካኝነት በቱሪስት ቪዛ ከአገር በወጡ የቤት ሰራተኞች ላይ የሚደርሰው የመብት ጥሰት አሳሰቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሌ ተናግረዋል። በቱሪስት ቪዛ የገቡ በመሆናቸው ከስድስት ወር እስከ ሁለት ዓመት አሰርተው ያለምንም ክፍያ ከቤት ተባረው በፖሊስ ተይዘው እየታሰሩ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ካሳሁን በአሁኑ ወቅት በቤይሩት 200 ሰራተኞች ታስረው እንደሚገኙ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀን የሚያደርጋቸው በረራዎች ተጓዦች 80 በመቶ በቱሪስት ቪዛ በህገወጥ ደላሎች የሚወጡ የቤት ሰራተኞች መሆናቸው ኮንፌዴሬሽኑ ይፋ አድርጓል። ሰራተኞቹ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት ጀምሮ እንደሆነ ያረጋገጠው ኮንፌዴሬሽኑ ከአገር ሲወጡም ከቀበሌ ዕድሜያቸው 22 ዓመት እንደሆነ የሚገልፅ መታወቂያ አግኝተው ፓስፖርት በማውጣት በቱሪስት ቪዛ ከአገር እንደሚያወጡ ማረጋገጡን ጠቁመዋል። በጊዜያዊነት ችግሩን ለመቅረፍ በቱሪስት ቪዛ የሚደረገው ጉዞ እንዲቆም፣ ከዕድሜያቸው 18 ሳይሞላቸው በመጨመር የቀበሌ መታወቂያ በሚሰጡ አካላት ላይ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ወላጆችም ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኮንፌዴሬሽኑ ጥሪ አቅርቧል። ከሊባኖስ ሰራተኛ ማህበራት ፌዴሬሽን ጋር በመሆን ከአገሪቱ በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረው የሚሰሩ ዜጎች መብትና ጥቅሞቻቸው እንዲከበርና የሚደርሱ ጥቃቶች እንዲቀንሱ እ.አ.አ ከ2015 ጀምሮ በጋራ እየሰራ ይገኛል። ኮንፌዴሬሽኑ ከሳውዲ አረቢያ፣ ኩዌት እና ባህሬን ጋር በአጠቃላይ የሰራተኞች መብት ዙሪያ የሁለትዮሽ ስምምነት የተፈራረመ ሲሆን ከሌሎች አገሮች ጋር ተመሳሳይ ስምምነት ላይ ለመድረስ እየሰራ ይገኛል። ኮንፌዴሬሽኑ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በኤርትራ ካለው አቻ የሰራተኞች ኮንፌዴሬሽን ጋር ግንኙነት ለመፍጠር በነገው ዕለት አንድ የልኡካን ቡድን ወደ ኤርትራ ይልካል። የልኡካን ቡድኑ አባላት ከኤርትራ የሰራተኛ ማህበራት ጋራ በመወያየት ግንኙነት የሚፈጥሩበት ዕድል እንደሚያመቻቹ አቶ ካሳሁን ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ የአፍሪካ ቀንድ የሰራተኛ ኮንፌዴሬሽን ለመመስረት የተያዘው ዕቅድ ላይ ልዑኩ እንደሚመክር ጠቁመዋል።