ቀጥታ፡

የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች አሸባሪው ህወሃትና ሸኔን በጋራ በመታገል ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን አስታወቁ

ባህርዳር ፣ የካቲት 03/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃትና ሸኔን በጋራ በመታገል ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ አቋም ይዘው በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች አሰታወቁ።

የሁለቱ ክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በባህርዳር ከተማ የግማሽ ቀን የጋራ ምክክር ካካሄዱ በኋላ  ርዕሳነ መስተዳድሮቹ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኦሮሚያ ከልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዴሳ በመግለጫቸው እንዳመለከቱት፤ የኢትዮጵያ አንድነት የሚረጋገጠው ጽንፈኛ ሃይሎችን በመታገል ማሸነፍ ሲቻል ነው።

ለዘመናት የዘለቀውን የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች  ትስስር አጠናክሮ በማስቀጠልም እንዲሁ።

ህዝብን ለማሸበር በማህበራዊ የትስስር ገፆችና ሌሎች መገናኛ አውታሮች የሚነዙ ጽንፈኛ አስተሳሰቦችን በአንድነት ታግሎ ለማስተካከል በምክክራቸው መግባባት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።

እስካሁን አሸባሪዎችን በጋራ በመታገሉ ሂደት የተገኙ  ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠልና  የተስተዋሉ ክፍተቶችን በማረም ሁሉንም ህዝብ እኩልነትና አንድነት ለማረጋገጥ በጋራ እንደሚሰሩ ነው አቶ ሽመልስ ያስታወቁት።

"በሀገራችን ውስጥ በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች በርካታ ህዝብ ተፈናቅሏል" ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ከሶስት  ዓመታት በላይ  በኦሮሚያ ክልል  ሰፊ ግጭት የተከሰተበት ሁኔታ መኖሩን አውስተዋል።

በግጭቱ የተፈናቀሉ ሰዎችን ቀድሞ ወደ ነበሩበት አካባቢ ለመመለስ ከሱማሌ፣ ቤንሻንጉል፣ ደቡብና አማራ ክልሎች ጋር በመተባበር በስፋት መሰራቱን አስታውሰዋል።

በቀጣይም የክልሉን ሰላምና መረጋጋት በማረጋገጥ ቀሪ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወደ ቦታቸው ለመመለስ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን  አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፍአለ በበኩላቸው የሀገርና የህዝቦች አንድነት ጸር የሆኑ ጽንፈኛ ሃይሎች ግጭት በመፍጠር፣ መንገድ በመዝጋት፣ ንጹሃንን በመግደልና በማፈናቀል እንዲራራቁና ከልማት እንዲስተጓጎሉ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እነዚህን ጽንፈኛ ሃይሎች በጋራና በአንድነት በመቆም ተዋግቶ በማሸነፍ የኢትዮጵያን አንድነት አስጠብቆ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለዚህም ሁለቱ ክልሎች  ጽንፈኛ ሃይሎችን  በጋራ ለመታገል አቋም መያዛቸውን አስታውቀዋል።

ሁለቱ ክልሎች በሚጎራበቱባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ዞኖችና ወረዳዎች ጽንፈኞችን በመታገልና በጋራ ላይ ልማት በማተኮር በጽናት ለመስራት መግባባት ላይ መድረሳቸውን ሁለቱ ርዕሳነ መስተዳድሮች አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም