ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን በአሸባሪው ህወሓት የወደመውን ሀብት ንብረት ወደ ነበረበት ለመመለስ እየተረባረቡ ነው

ባህር ዳር፣ የካቲት 03/2014(ኢዜአ)  በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሓት የወደመውን ሀብት ንብረት ወደ ነበረበት ለመመለስ ኢትዮጵያውያን በሚችሉት ሁሉ ድጋፍ በማድረግ እየተረባረቡ ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፍአለ ገለጹ።

የሽብር ቡድኑ በአማራ ክልል ያደረሰውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ሀብት መልሶ ለመገንባት እየተደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ጥረት ለማገዝ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ዛሬ የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር ይልቃል በርክክብ ሥነስርዓቱ ላይ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት የከፈተው ጦርነት የኢትዮጵያን አንድነት ለማፈራረስ በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን ህብረታቸውን አጠናክረው ወረራውን በጋራ መክተዋል።

የጥፋት ቡድኑ በአማራ ክልል በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች ሁሉ ንጹሃንን በግፍ በጅምላ በመግደል፣ ሴቶችን በመድፈርና በማቁሰል የፈጸመው ግፍ መቼም የማይጠፋ ጥቁር ጠባሳ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሽብር ቡድኑ የወደመውን ሀብትና ንብረት ወደ ነበረበት ለመመለስ መላው ኢትዮጵያውያን እየተረባረቡ ነው ብለዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድነትና ሕብረቱን አጠናክሮ በሚችለው ሁሉ በአይነትና በጥሬ ገንዘብ እየደገፈ መሆኑን ዶክተር ይልቃል  አስረድተዋል።

"በውጭ ሀገር የሚኖሩ ዳያስፖራዎችም በመልሶ ግንባታና ማቋቋም ሥራው ከጎናችን ቆመዋል" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ዓለም የህወሓትን የጥፋት ተግባር ዘግይቶም ቢሆን እየተረዳ መምጣቱን ተናግረዋል።  

አሸባሪው ህወሓት ጦርነቱን ሲጀመር ሀገር ለማፍረስ ቆርጦ የመነሳቱን እውነት ሁሉም ስለመረዳቱ በጦርነቱና በመልሶ ማቋቋሙ ኢትዮጵያዊያን እያደረጉት ያለው ድጋፍ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ ዶክተር ይልቃል ገለጻ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላትን ለመመከት በተካሄደው ውጊያ በገንዘብ፣ በቁሳቁስና በስነልቦና ድጋፍ በማድረግ አብሮነቱን በተጨባጭ አሳይቷል፤ አሁንም እያሳየ ነው።

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥትም የኢትዮጵያን አንድነት ለማፅናት አሸባሪው ህወሓት ጥቃት መፈጸም ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ልዩ ኃይሉን በመላክ ከሀገር መከላከያና የፀጥታ ኃይሎች ጎን በመሰለፍ አጋርነቱን በተግባር ማሳየቱን ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው "አሁን የምናካሂደው ትግል ከአሸባሪዎቹ ህወሓት፣ ሸኔና ሌሎች ጽንፈኛ ቡድኖች ጋር መሆኑን መገንዘብ ይገባል" ብለዋል።

በኦሮሚያ  ክልል ቦረና እና ጉጂ ዞኖች የተከሰተው ድርቅ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ ክልሉ በብዙ ችግር ውስጥ መሆኑን አመልክተዋል።

"በዚህ ችግር ውስጥ ብንሆንም በአማራ ክልል የደረሰውን ጉዳት ለመደገፍና ከጎናችሁ በመቆም ነባሩን የእርስ በርስ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴት ለማጠናከር ድጋፍ ይዘን እዚህ ተገኝተናል" ብለዋል።

"በክልሉ በሚያካሂደው የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ አብረን ለመስራት የኦሮሚያ ክልል መንግሥትና አመራር ወስኗል" ያሉት አቶ ሽመልስ፣ "በቀጣይም ተባብረንና ተረዳድተን  የገጠመንን ችግር መቋቋም አለብን" ብለዋል።

በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት በአቶ ሽመልስ አብዲሳ  የተመራው ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት አቻው ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መክሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም