አሸባሪው ህወሃት ውድመት ያደረሰባቸው ሆቴሎችና የቱሪዝም መዳረሻዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ንቅናቄ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሃት ውድመት ያደረሰባቸው ሆቴሎችና የቱሪዝም መዳረሻዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ንቅናቄ ተጀመረ
የካቲት 3/2014/ኢዜአ/ አሸባሪው ህወሃት በአማራና በአፋር ክልሎች ውድመት ያደረሰባቸውን ሆቴሎችና የቱሪዝም መዳረሻዎች መልሶ ለማቋቋም ”በሙያዬ ለአገሬ” የተሰኘ የንቅናቄ ዘመቻ ተጀመረ።
የኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ አሰሪዎች ፌደሬሽን ”በሙያዬ ለአገሬ” ንቅናቄን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫውም የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍትህ ወልደሰንበት፤ አሸባሪው ህወሃት በወረራ በቆየባቸው አማራና አፋር ክልሎች በሆቴሎችና በቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል።
በዚህም በዘርፉ ላይ ተሰማርተው አገልግሎት የሚሰጡ አካላት ከሥራ ውጭ እንዲሆኑና ተቋማቱም በሙሉ አቅማቸው እንዳይንቀሳቀሱ አድርጓል ነው ያሉት።
ፌደሬሽኑ እነዚህን ሆቴሎችና የቱሪስት መዳረሻዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ ከበጎ ፈቃደኛ የሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ጋር እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።
በዚህም 286 የሚሆኑ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች፣ በመንግሥትና በግል የሚንቀሳቀሱ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ”በሙያዬ ለአገሬ” የተሰኘ ንቅናቄ መጀመሩን ገልፀዋል።
እነዚህ የዘርፉ ባለሙያዎች በቅድሚያ በስድስት ቡድን በማዋቀር በዘርፉ የደረሰውን ጉዳት ምንድን ነው የሚለውን በአካል ተገኝተው የዳሰሳ ጥናት እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።
ከዛም በኋላ እነዚህ ሆቴሎችንና የቱሪስት መዳረሻዎች አስፈላጊው የቁሳቁስና ሌሎች ሙያዊ እገዛ የሚያገኙበትን ሁኔታዎች የመፍጠር ሥራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
ንቅናቄው በዋናነትም ሆቴሎችንና የቱሪስት መዳረሻዎች የማደራጀት፣ የማማከር፣ የሥልጠናና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ወደ ሥራ ለመመለስ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።
በንቅናቄው ሸዋሮቢት፣ ከሚሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴ፣ ወልዲያ፣ ላልይበላ፣ ጭፍራና ካሳጊስታ የሚገኙ ሆቴሎችንና የቱሪስት መዳረሻዎች ይሸፈናሉ ብለዋል።
ዘመቻውም ከግብ እንዲደርስ በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ባለሆቴሎችና ሌሎች የዘርፉ አካላቶች የተለያዩ እገዛዎችን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።