የዋጋ ንረትን ለመከላከል ሸማችና አምራቹን በቀጥታ የማገናኘት ሥራ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዋጋ ንረትን ለመከላከል ሸማችና አምራቹን በቀጥታ የማገናኘት ሥራ እየተሰራ ነው
የካቲት 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዋጋ ንረትን ለመከላከል ሸማችና አምራቹን በቀጥታ የማገናኘት ሥራ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ገለጸ።
ኮሚሽኑ ''ለሰላምና ለተረጋጋ ገበያ'' በሚል መሪ ኃሳብ በአዲስ አበባ ኢግዚቤሽንና ገበያ ማዕከል ለአምስት ቀናት የሚቆይ የንግድ አውደ ርዕይ አዘጋጅቷል።
የኮሚሽኑ ተወካይ አቶ ዳረቦ ቡሴራ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የምግብ ፍጆታዎች ዋጋ ለማረጋጋት ሸማቹንና አምራቹን በቀጥታ የማገናኘት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
በአዲስ አበባ ዋና ዋና መዳረሻዎች የሚገኙት የኅብረት ሥራ ማኅበራትና የእሁድ ገበያዎች የኑሮ ውድነት በማቃለል አዎንታዊ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዛሬ የተከፈተውም የንግድ አውደ ርዕይ የግብርና ምርቶችና የተለያዩ የፍጆታ እቃዎች በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።
የግብርና ምርትን ለማሻሻል፣ የተረጋጋ የግብርና ምርቶች ግብይት ሥርዓትን ለማጠናከርና የሸማቹን ተጠቃሚነትን ለማሳደግም አስተዋጽዖ እንዳለው ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ የንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ፤ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በማሳደግ ከውጪ የሚገቡ መሰረታዊ ፍጆታዎች በአገር ውስጥ ለመተካት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለዚህም ለአገር ውስጥ አምራቾች ዘላቂ የገበያ ትሰሰር በመፍጠርና ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት።
አርሶ አደሩ ምርቱን በጥሬው ከመሸጥ እሴት ጨምሮ በሚፈልገው መጠን አዘጋጅቶ ማቅረብ ላይ የተጀመሩ ሥራዎች የሚበረታቱ መሆኑን ጠቁመዋል።
የምግብ ፍጆታ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ በአዲስ አበባ የተጀመረው የእሁድ ገበያ ጥሩ ጅማሮ ማሳየቱን ገልጸው ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
እንደነዚህ ያሉ የንግድ አውደ ርዕዮች በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ቶሎ ቶሎ ሊዘጋጁ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
በኢግዚቢሽኑ በመላው የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ 138 ኅብረት ሥራ ማኅበራትና ከ38 በላይ የኢንዱስትሪ ምርት አቅራቢዎች ይሳተፋሉ ተብሏል።