አመራሩ በምርጫ ወቅት ለህዝቡ የገባውን ቃል ለመፈጸም በትብብር መስራት ይጠበቅበታል

37

ሚዛን፣ የካቲተ 03/2014 (ኢዜአ)አመራሩ በምርጫ ወቅት ለህዝቡ የገባውን ቃል ለመፈጸም በጊዜ የለንም መንፈስ በትብብርና እና በአንድነት መስራት እንደሚጠበቅበት ተመለከተ።

የብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል  ጽህፈት ቤት  ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ማሞ   "መመረጥ - ተለውጦ ሀገርን ለመለወጥ"በሚል መሪ ሀሳብ  በክልሉ  ለሚገኙ የፓርቲው አመራሮችና አባላት  እየተሠጠ ያለውን የአቅም ግንባታ መድረክ አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው እንዳመለከቱት፤ ህዝቡ በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለብልጽግና ፓርቲ የሰጠውን ይሁንታ በላቀ ደረጃ ለመፈጸም  የአመራሩን  አቅም ማጎልበት ያስፈልጋል።

ከዚህ አንፃር በንቁ ተሳትፎና በዲሞክራሲያዊ የትግል ምዕራፍ፣እንዲሁም  የፖለቲካና የውስጠ ፓርቲ ዙሪያ ያተኮረ የአቅም ግንባታ መድረክ በክልሉ ለሚገኙ አመራሮች መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በመድረኩም የሠላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር  ችግሮችን የሚያቃልልና ክፍተቶችን ለመሙላት የሚችል አመራር ለመፍጠር የጎላ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።

ፓርቲው አመራሩን በየደረጃው በማጥራት እና መልሶ በማደራጀት የተሠጠውን ተልዕኮ በአግባቡ  መወጣት የሚችል ብቃት እና ጥራት ያለው ለማድረግ  አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በየደረጃው የሚገኘው አመራር እራሱናሌላውንም በማብቃት የአመራርነት ስብዕና  እንዲጎለብት ማስቻል ይጠበቅበታል ብለዋል።

በተለይ አመራሮች ፖለቲካዊ እይታቸው እንዲጠራ በማድረግ፣ ውጤታማነታቸውና  አጋልጋይነታቸውን በማሻሻል የህዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች  ለመመለስ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ለዚህ እውን መሆን ከጥር 24  እስከ 27/2014 ዓ/ም  ለክልል ማዕከል የተሰጠውን የከፍተኛ አመራሮች ሥልጠና በማስቀጠል በዞን፣ በወረዳና በከተማ አስተዳደር  ደረጃ ለሚገኙ አመራርና  አባላት እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተደበላለቀ  ስሜትና በተዛባ አስተሳሰብ ታጥሮ የሚፈልገውን ለውጥ ማምጣት ስለማይቻል የመድረኩ ተሳታፊዎች በአስተሳሰብ እና  በአመለካከት የጠራ አቋም ይዘው መውጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በምርጫ ወቅት ለህዝቡ የገባውን ቃል ለመፈጸም  በጊዜ የለንም መንፈስ በትብብርና እና በአንድነት መስራት   በየደረጃው ከሚገኝ አመራር እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

ክልሉ ከብልጽግና ፓርቲ ትሩፋት መካከል አንዱ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው፤ በተለይ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው በርካታ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኝ  ጠንክሮ መስራት  እንዳለበት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም