በጎ ፍቃደኞች ለድርቅ ተጎጂዎች የእንስሳት መኖ ድጋፍ አደረጉ

60

የካቲት 03 / 2014 (ኢዜአ)  በጎ ፍቃደኞች ባሰባሰቡት ገንዘብ በቦረና ዞን ለድርቅ ተጎጂዎች የእንስሳት መኖ በመግዛት ድጋፍ አደረጉ።
በዚህ ዓመት ድርቅ በተከሰተባቸው የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ይታወቃል።

በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የተከሰተው ድርቅ በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ችግር እያስከተለ ይገኛል።

የድርቁ ተጎጂዎች ለመደገፍ የድርሻችንን እናበርክት ብለው የተነሱ 42 በጎ ፈቃደኞች ገንዘብ በማሰባሰብ ለአርብቶ አደሮች የእንስሳት መኖ ድጋፍ አድርገዋል።

የድጋፉ አስተባባሪ አቶ መስፍን ሃይሉ፤ ድርቁ በቦረና ዞን በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን በመገንዘብ የድርሻችንን አስተዋፅኦ ለማድረግ ተነጋግረን ገንዘብ ማሰባሰብ ችለናል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ውጭ ከሚኖሩ ወገኖች ከ400 ሺህ ብር በላይ በማሰባሰብ የእንስሳት መኖ በመግዛት ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ በእንዲህ አይነት አስቸጋሪ ወቅት በችግር ላይ የሚገኙ ወገኖችን የቻልነውን ሁሉ እገዛ ማድርግ አለብን ብለዋል።

በኦሮሚያና ሶማሊያ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በሰዎችና እንስሳት ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር ለማቃለል ተባብረን እንደግፋቸው በማለትም ጥሪ አቅርበዋል።

ድጋፉን ለማድረስ በስፍራው የተገኙት ወጣቶቹ ድርቁ በተለይም በእንስሳት ላይ ያደረሰውን ጉዳት በተመለከቱ ጊዜ ማዘናቸውን ገልጸው ሁላችንም ልንደርስላቸው ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም