ቀጥታ፡

አሸባሪው የህወሃት ቡድን በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት አውድሟል

አዲስ አበባ የካቲት 2/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ማውደሙን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
የሽብር ቡድኑ በአማራና አፋር ክልል ከሚገኙ ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች መካከል ከ53 በመቶ በላይ በሚሆኑት ላይ ጉዳት ማድረሱም ተገልጿል፡፡

የተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን፤ የሽብር ቡድኑ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ያደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የሽብር ቡድኑ በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች 53 በመቶ በላይ በሚሆኑ ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ጉዳት መድረሱን አንስተው፤ በዚህም በአካባቢዎቹ ያሉ ነዋሪዎች ከ14 ቀን እስከ 6 ወር ለሚደርሱ ጊዜያት ኤሌክትሪክ እንዳያገኙ ማድረጉን ተናግረዋል።

የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ የደረሰው ጉዳት የውሃ፣ ቴሌኮም፣ ህክምና እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶችን ማስተጓጎሉንም ገልፀዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ከጉዳት ባሻገር በተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ስርቆት መፈፀሙንና  የድምፅና ዳታ ማስተላለፊያ ኦፕቲካል ፋይበር ላይ ጉዳት ማድረሱንም አስረድተዋል።  

የሽብር ቡድኑ በአምስት የተለያዩ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች እንዲወድቁ መደረጉን ጠቅሰው፤የተለያዩ መለዋወጫ እቃዎችን መዘረፉንና ማውደሙንም ተናግረዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች በአጠቃላይ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በሚያወጣ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ጉዳት ማድረሱንም ነው የገለጹት፡፡

እስካሁን ባለው ሂደት 29 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የጥገና ስራ በማከናወን አካባቢዎቹ ኃይል እንዲያገኙ መደረጉንም አንስተዋል፡፡

በደረሰው ጉዳት ሳይሸጥ የባከነ ኤሌክትሪክ ተቋሙን 231 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማሳጣቱንም ነው ያብራሩት፡፡

በተደረገው ጥገና አብዛኛዎቹ የአማራና አፋር አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት መቻላቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ጉዳት የደረሰባቸውን የኃይል መቆጣጠሪያ ጣቢያዎችን ወደ ቀድሞ አቅማቸው በመመለስ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲሰጡ ለማድረግ ቀጣይ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም